ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት ጋር በኢንቨስትመንት ዙሪያ ተወያዩ

ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢንቨስትመንት አቅም ዙሪያ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት  ጋር  በአርባምንጭ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የክልሉ መንግስት የክልሉን ዕድገት እና ልማት ለማፋጠን ልዩ ትኩረት ካደረገባቸው ዘርፎች አንዱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ክልሉ በርካታ ፀጋዎችና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያለው መሆኑን ተናግረው የክልሉ መንግስት ክልሉን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹና ተስማሚ በማድረግ ባሉት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶችን ለመሳብ በርካታ ስራዎችን መስራቱም አብራርዋል፡፡

በውይይቱ የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅምና አማራጮች በተመለተ በክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ  ኃላፊ  ኦንጋዬ ኦዳ (ዶ/ር) ሰፊ ገለፃ ተደርጓል።

ኃላፊው በማብራሪያቸው ክልሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አመራጮች ያሉት መሆኑን ገልፀው በተለይም በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፤ በአገልግሎት፤ በማዕድንና ለሎች ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ መመቻቸቱን አብራርተዋል፡፡  

የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት በተደረገላቸው ገለፃ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ የክልሉን ኢንቨስትመንት አቅም ምልከታ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች የቻይና ኢንቨስተሮች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ በኢትዮጵያ የቻይና ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱም የተገለፀ ሲሆን፤ የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነትና ትብብር በተለይ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱም ተብራርቷል፡፡ 

የኮሚቴው ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱ በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ያሉ ትብብሮች እያደገ መምጣቱ በኢትዮጵያ በማንፋክቸሪንግ እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ጉልህ አስትዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሊቀ-መንበሯ አያይዘው ትብብሩን በማጠናከር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በዘርፉ የቻይና ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፍላጎት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ክልሉን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹና ሳቢ በማድረግ ተጨማሪ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በተለይ በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፤ በአገልግሎት እና ሌሎች ዘርፎች ለመሳብ የህግና የአሰራር ማሻሻያ ማዕቀፎችን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑም በውይይቱ ተገልጿል፡፡

የኮሚቴው አባላት አርባምንጭ አለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በክልልና በዞን ከፍተኛ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

Leave a Reply