ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለቡርጂ ብሔረሰብ የምስጋናና የዘመን መለወጫ የ “ዎናንካ አያና” በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት አስተላልፈዋል

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለቡርጂ ብሔረሰብ የምስጋናና የዘመን መለወጫ የ “ዎናንካ አያና” በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት አስተላልፈዋል፡፡ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ዮያ ቡርጄ!  ዮያ ዳሾ!  ዮያ ጉል ጉባ!

ባጋ ዳንሳሽን፤ ዎናን’ካ አያናጋ ዳቃሳንችንኩ

እንኳን አደረሳችሁ! እንኳን አደረሰን!

ታታሪነት መገለጫው፤ ሰላም ወዳድነት፤ እንግዳ ተቀባይነትና ደግነት መለያው፤ በህብረት መትጋትና ተጋግዞ ማደግ ባህሉ፤ የነጭ ማኛ ጤፍ እና ቡራ ቡርጅ ቦሎቄ አምራች፤ በሚንሞና ዋሻ፤ በዲቃቼ ፋፋቴ፤ በክሊቾ መሃላ ድንጋይ፤ በሙሬ ታሪካዊ ተራራ፤ በዎዮ ደን እና በርካታ ድንቅ መስህብ ባለቤት ለሆነው ቡርጂ ብሔረሰብ የምስጋናና የዘመን መለወጫ የ”ዎናንካ አያና” በዓል እንኳን አደረሰን! አደረሳችሁ!

“ዎናንካ አያና” የበርካታ ድንቅ እሴቶችና ፀጋዎች ባለቤት የሆነው የቡርጂ ብሔረሰብ በራሱ የጊዜ ቀመር በወርሃ የካቲት መባቻ ከዘመን ዘመን በሰላም መሸጋገሩን በማብሰር የሚያከብረው ልዩ የምስጋና በዓል ነው፡፡

በቡርጂ ህዝብ ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ‘ዎና’፤ የላቡን ፍሬ ባርኮ ምርት ለሰጠ፤ ያመረተውን ምርት ሰብስቦ በጎተራው እንዲያስገባ ለረዳ፤ አመቱን በሙሉ በሁሉ ነገር ለደገፈና ላገዘ ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብና መጪው አዲስ ዘመንም የሰላም፤ የአንድነትና የበረከት እንዲሆን በመመኘት በምርቃት የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ባህላዊ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ የሚከበረው በዓሉ፤ የህዝቡን አብሮነትና አንድነት በሚያጠናክሩ ስርዓቶች፡- ‘በጭሙንታታ ሴራ’፤ በውብ የ’ግርዝ’ ባህላዊ ጫወታ እና በ’ዎና’ ዘፈን ደምቆ፤ የተለያዩና የተነፋፈቁ ከያሉበት ተሰባስበው በፍቅር የሚያከብሩት የአብሮነት በዓል ነው፡፡   

በ’ዎና’ ሰላምና ፍቅር ያይላል፣ አንድነትና አብሮነት ይበልጥ ይጐለብታል፤ መተሳሰብና መረዳዳት በእጅጉ ጎልቶ ይወጣል፣የህዝቡ ትስስርና ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያለው ወንድማማችነት ይፀናል፡፡

“ዎናንካ አያና” የዕርቅ፤ የመታነፅና የመሻገር ተምሳሌት ነው!

የተቀያየሙ የሚታረቁበት፤ ቅምና ቁርሾ በይቅርታ ተሽሮ ሰላም የሚያብብበት፤ ባለፈው አመት የነበሩ ድክመቶችን አርመው፤ ስህተቶችን አሪቀውና ውስንነቶችን አልቀው በ”አግናይሼ ስርዓት” በመታነጽ፤ በተሻለ ምግባርና ሥራ ለተሻለ ስኬት ራስን በማዘጋጀት በብሩህ ተስፋ ተሞልተው ወደ አዲሱ ዘመን የሚሻገሩበት ድንቅ የክልላችን እሴት ነው፡፡

የታታሪነትና የጠንካራ ሥራ ወዳድነት ምልክት የሆነው “ዎና”፤ ቡርጂዎች የመኸር አዝመራ ምርታቸውን ሰብስበው ከድካማቸው ፍሬ በመቋደስ እፎይ የሚሉበት ብቻ ሳይሆን፤ ባገኙት ምርት ሳይዘናጉ በአዲስ ጉልበትና በመታደስ መንፈስ ለምርት ዘመኑ የበልግ አዝመራ ዝግጅት የሚያነሳሳ የጎላ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው በዓል ነው፡፡

በዓሉን ስናከብር ብዙ መስራትና ብዙ ማልማት በሚጠበቅብን በዚህ ወቅት፤ የታታሪነት መገለጫ ከሆነው ዎና ብዙ ትምህርት በመውሰድ ባስመዘገብናቸው ስኬቶች ሳንኩራራ፤ ህብረትና አንድነታችንን አጠናክረን ለላቀ ውጤት በመትጋት በማያቋርጥ ጥረት ብልፅግናችንን ለማረጋገጥ በመነሳሳት ሊሆን ይገባል፡፡  

ከትውልድ ትውልድ ስሸጋገር የመጣው ‘ዎና’፤ የማህበረሰቡ የማንነት መገለጫ የሆኑ የህብረትና የወንድማማችነት እሴቶች የሚጎሉበት በመሆኑ፤ የህዝቦች ትስስርንና ትብብርን የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ ለብሔረሰቡ የባህል ሀብት ልማትና ለአካባቢው ዕድገት አስትዋጽኦው የጎላ ነው፡፡ 

በመሆኑም አባቶች ያቆዩልንን ይህን ድንቅ እሴት፤ ትውልዱ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት የበዓሉን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ እሴቶች ከነሙሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ሰንዶ ለማሻገር መስራት ይጠበቅበታል፡፡   

በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ!!

ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር

Leave a Reply