ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን፤ በካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በስፍራው በመገኘት አጽናንተዋል።
በክልሉ ወላይታ ዞን በካዎ ኮይሻ ወረዳ የተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በማጽናናት በተከሰተው ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ ለጠፋው የውድ ወገኖች ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመሆን በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
አክለውም በአካባቢው እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተያይዞ መሰል አደጋ ተከስቶ ጉዳት እንዳያደርስ የተጀመሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ከዞኑ አስተዳደር እና ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት አፋጣኝ የአደጋ ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው በክልሉ ከወቅቱ የክረምት ዝናብ ጋር ተያይዞ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል አደጋዎች የተከሰቱና በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉ በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተለይ የአደጋ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች በየደረጃው ያለው አመራር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ አጠናክሮ መስራት እንደሚገባውም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
በአደጋው ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች የማስጠለል ተግባርም የተከናወነ ሲሆን፤ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ስራ በመሰራት ላይም ይገኛል፡፡
ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም በስፍራው ተገኝተው በአደጋው ምክንያት ባለፈው የዜጎች ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል።