“የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለይቶ ለመፍታት በትኩረት መስራት ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ጥራትና ግብይት ቁጥጥር አስተባባሪ ግብረ ሀይል የ2017 ግማሽ ዓመት የቡና ጥራት አጠባበቅና አቅርቦት ዙሪያ በወላይታ ሶዶ ከተማ ውይይት አኳሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የለውጡ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲውን ከአንድ ዘርፍ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ሲያሻግር፥ ግብርናን ዋነኛ የኢኮኖሚው መሠረት በማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስትም ግብርናን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የክልሉ ኢኮኖሚ መሠረት በማድረግ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የኤክስፖርት ምርቶች በማምረት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የክልሉን እምቅ አቅም በመለየትና በመጠቀም የቡና እና ቅመማ ቅመም ምርት ጥራትና ምርታማነት በማሳደግ ወደ ውጪ መላክ ቀዳሚ ተግባር በማድረግ በመስራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ቡና በሀገራችን የአረንጓዴ ወርቅ የሚል ስያሜ የተሰጠው፤ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠራ ሰብል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቡናን በማምረት ከሚገኘ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተጨማሪ በገዢና አምራች መካከል ጤናማ ግንኙነት በመፍጠር በማህበራዊ ዘርፉ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ክልሉ የይርጋጨፌ፥ የአማሮ እና ሌሎችም ባለ ልዩ ጣዕም ጥራት ያላቸው ቡናዎች የሚበቅሉበት መሆኑንም ገልፀው፤ ዘርፉ የውጪ ምንዛሬ በማስገኝት ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ቡናን ክልሉ ባለው አቅም ልክ በማምረት ኤክስፖርት ከማድረግ አንፃር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቡና ማሳን በማስፋት እና በኩታ ገጠም በማረስ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪ ቡናን በስፋት ለማምረት የቡና ኤክስቴሽን ስራዎችን በአግባቡ መምራት እና መተግበር እንዲሁም ህገ ወጥ የቡና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለው የቡና ማሳን በማስፋትና በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ቡና በማምረት አርሶ አደሩ ባመረተው ልክ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ታአማኒ፥ በገበያ ተፈላጊና ተወዳዳሪ የሆነ ጥራት ያለው ቡና በደቡብ ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በስፋት እንዲመረት የቡና ጥራትና ግብይት ቁጥጥር አስተግባሪ ግብረ ሀይሉ ተጠናክሮ በመስራት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

ዘርፉ መሰረታዊ ማነቆዎች ያሉት መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የቡና ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳ በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለይቶ ለመፍታት በትኩረት መስራትና የባህል እጥፋት በማምጣት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል።  

በቅርቡ በኢትዮ ቻይና የልማት ትብብር በተፈጠረ የንግድ ትስስር ጥራት ያለው የይርጋጨፌ ቡና ወደ ቻይና ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፥ ተሞክረው ወደ ሌሎች ቡና አምራች አካባቢዎች መስፋት ይኖርበታል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ማነቆዎችን በመፍታት ምርታማነትን ለማሳደግ ባነሷቸው ነጥቦች፡-

የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መድረክ መፍጠርና የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት፣ የቡና ማሳን ማስፋትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ተግባራትን በትኩረት መከወን እንዲሁም የምርት ግብየትን ጤናማና ሰላማዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለመካናይዝድ እርሻ የኢንቨስትመንት መሬቶችን በማዘጋጀትና የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የክልሉን የቡና ምርታማነት ለማሳደግ መስራት ይገባል በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

በምክትል ርዕለ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ ( ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ክልሉ ቡናን ኤክስፖርት በማድረግ ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

አክለው የቡና ምርት በሁሉም ስነምህዳሮች የሚበቅል ብቻ ሳይሆን በእርሻ ላይ ለሌሎች የግብርና ስራዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሰብል መሆኑን ተናግረው፥ በክልሉ በ2017 25 ሺህ 884 ቶን ቡና ለገበያ መቅረቡን አስታውቀዋል።

Leave a Reply