በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የፓርቲው ከፍተኛ የአመራሮች ልዑክ በጎፋ ዞን በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በማፅናናት የ20 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ እጅግ ልብ ሰባሪና እና አስከፊ መሆኑን ገልፀው፤ ለአደጋው ተጎጂዎች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
አደጋው ከኢትዮጵያ አልፎ አለምን ያስደነገጠ መሆኑን የተናገሩት አቶ አደም ፋራህ፤ በአደጋው እጅግ ብናዝንም አደጋውን ተከትሎ የታየው መደጋገፍ የኢትዮጵያ ህዝብን የመረዳዳት ባህል አጉልቶ ያሳየ እና የሚመሰገን መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ አደም ፋራህ አያይዘው ብልፅግና ሰው ተኮር ፓርቲ ነው ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የፓርቲው ጽ/ቤት እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በጋራ የ20 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት እንደ ፓርቲ መደገፋችን ይቀጥላል ያሉት አቶ አደም ፋራህ፤ በዚህ የፓርቲውን ለዜጎች ያለውን ተቆርቋሪነት ያሳየ የሰብአዊነት ተግባር ላይ የተሳተፉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን አመስግነዋል።
አቶ አደም ፋራህ በጎፋ ዞን በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሳቢያ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክትም፡- “ስንተባበርና በአንድ ላይ ስንቆም፣የአንዳችን ቁስል የአንዳችን ህመም ሲሆን፣ በጋራ የመዳን ተስፋችን ይለመልማልና ሁሌም ለመረዳዳት፣ለመተጋገዝ፣ለወንድማማችነት እና ለእህትማማችነት እሳቤ መዳበር የበኩላችንን ሚና እንወጣ!!” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሮች አደጋው ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ ክትትል በማድረግ በሀሳብ ሲደግፉ መቆየቱን ገልፀው፤ ለተደረገው ድጋፍ በክልሉ ህዝብ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ክስቱት ሰው ለማዳን የተከፈለ የህይወት ዋጋ መሆኑን አስታውሰው፤ አደጋው ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ከፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ ሁሉም አመራሮች ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን ሀዘናችንን ስለተጋራችሁ እና ድጋፍ ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው የክልሉ መንግስት የአደጋው ተጎጂዎችን በቋሚነት ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑን አስረድተው፤ በፓርቲው የተደረገው ድጋፍ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡