የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በ4ኛ መደበኛ ጉባኤው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አፀደቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት የቀረቡለትን ስድስት አዋጆች እና አንድ ፖሊሲ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

እነዚህም፡-

1- የክልሉን የሪጅዮ ፖሊስ ከተሞች ለማደራጀት የወጣ አዋጅ፤

2- የኢንቨስትመንት አስተዳደርን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ፤

3- የ2017 ዓ.ም ተጨማሪ የበጀት ረቂቅ አዋጅ (በ2017 የማክሮ ኢኮኖማ ማሻሻያ ተከትሎ ዝቅተኛ የኑሮ ጫና ያለባቸውን ህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ለተደረገው የደምወዝ ጭማሪ ከፌደራል መንግስት የተላከ በጀት ማስተዳደሪያ ረቂቂ አዋጅ)፤

4- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ለማቋቋም የወጣ አዋጅ፤

5- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ዉሃ ተጠቃሚዎች ማህበር አዋጅ፤

6- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰንደቅ ዓላማና አርማ ለመደንገግ የወጣ አዋጅ፤

7- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበጎ ፍቃደኝነት ረቂቅ ፖሊሲ፤

ምክር ቤቱ ከላይ በተጠቀሱ ረቂቅ አዋጆች ላይ በመምከር ከተሰጡ ማሻሻያዎች ጋር በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

በዚህም የክልሉ መንግስት የ 2017 ዓ.ም ተጨማሪ በጀት 4 ቢሊዮን 204 ሚሊዮን 419 ሺ 219 ብር ሆኖ የቀረበው ረቂቅ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።

በምክር ቤቱ ከፀደቁት አዋጆች አንዱ፤ የክልሉን የሪጅዮ ፖሊስ ከተሞች ለማደራጀት የወጣ አዋጅ ሲሆን፤ ይህም ወላይታ ሶዶ፤ አርባ ምንጭ እና ዲላ ከተሞች በክልሉ በሪጂዮ ፖሊስ ደረጃ እንዲደራጁ ለከተሞቹ ትልቅ ዕድል የፈጠረ አዋጅ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ በተወያየበት ወቅት፤ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፡-

በሪጂዮ ፖሊስ የሚደራጁ ከተሞች ተጠሪነታቸው ለክልል መሆኑ ዞኖች ላይ የሚኖረውን ጫና የሚቀንስ ብቻ  ሳይሆን፤ ከተሞች በተሻለ ፈጣን የእድገት ጎዳና እንዲጓዙ እና ከአለማቀፍ እህት ከተሞች ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማስቻል የተሻለ የኢኮኖሚ፤ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲሲቡ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

በዚህም የሪጅዮፖሊስ ከተማ አደረጃጀት የዞንንም ሆነ የከተማው ነዋሪን በዘርፈ ብዙ መንገዶች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን እና ለሌሎች የክልሉ ከተሞች ዕድገትም አስትዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየትም ከተሞችን በሪጂዮፖሊስ ማደራጀት በክልሉ ለሚገኙ ከተሞች ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠር ዕድገታቸውን የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከተሞች የኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና የማህበራዊ ሽግግር ማዕከላት እንዲሆኑ በማስቻል የሌሎች በዙሪያ የሚገኙ ከተሞች ዕድገትንም የሚያፋጥንና የተጀመረውን የብልፅግና ጎዞ የሚያሳልጥ መሆኑ ተገልጿል።

Leave a Reply