ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ አመት ታሪካዊ የምስረታ ክብረ በዓል “ከነሐሴ እስከ ነሐሴ” በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክልሉ ሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ህዝበ ውሳኔ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደ ታሪካዊ የምስረታ ጉባኤ የፌደሬሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ በይፋ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
ክልሉ በረዥም ዘመን አብሮነት የተጋመዱና የተሳሰሩ 32 ነባር ብሔረሰቦችና ሌሎች ሕዝቦች ነፃ ፈቃድ ቀዳሚው የብዝኀ ሕዝቦች ክልል ሆኖ ከተመሰረተ አንድ አመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ የክልሉ የ1ኛ አመት የምሰረታ ክብረ በዓል የክልሉን የአንድ አመት ጉዞ በጥልቀት በዳሰሰ መልኩ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በክብሬ በዓሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በይፋ መርቀው የከፈቱት በክልሉ የአንድ አመት ጉዞ የተከናወኑ አንኳር ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩኔቶች የሚያስቃኝ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን ቀርቦ በተሳታፊዎች ተጎብኝቷል፡፡
በመርሃ ግብሩ በክልሉ የምስረታ ጉባኤ ወቅት የፀደቀው የክልሉ ሕገ-መንግሥት የርክክብ ሥነ-ሥርዓትም የተካሄደ ሲሆን፤ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በነጋሪት ጋዜጣ እና በመፅሃፍ ተሰንዶ የተዘጋጀ የክልሉ ሕገ-መንግሥት ለክልሉ ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ለወ/ሮ ፀሀይ ወራሳ አስረክበዋል።
የክብረ በዓሉ ዋነኛ አካል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “ከነሐሴ እስከ ነሐሴ” በሚል ርዕስ የክልሉን የቅድመ-ምስረታ፣ ምስረታ እና የድህረ-ምስረታ ሂደት እና በክልሉ የአንድ አመት ጉዞ የተከናወኑ ዐቢይት ተግባራት የሚዳስስ ፁሁፍ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት ፁሁፍ በክልሉ የአንድ አመት ጉዞ የተሰሩ የሽግግርና መደበኛ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች፤ የተመዘገቡ ስኬቶች፤ የተፈጠሩ መልካም ዕድሎች እንዲሁም ያጋጠሙ ውስንነቶችንና ችግሮች ከተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ጋር በስፋት ዳሰዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ክልሉን ከማደራጀት ጀምሮ በሁሉም አውታሮች በተሰሩ ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉ የተመለከተ ሲሆን፤ ይህንኑ ለቀጣይ መስፈንጠሪያነት በመጠቀም ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ጎዞን የክልሉን ህዝቦች በንቃት በማሳተፍ በክልሉ ፈጣን ዕድገት፤ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ ከርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተጨማሪ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎችና አባላት፤ የዞን አመራሮች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች፤ ምሁራን እና ሌሎች ተጋባዥ ዕንግዶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።