“የ2017 ዓ.ም የበጀት ድልድል ረቂቅ ቀመር ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችንና የክልሉን ህዝብ በጋራ የመልማት ፍላጎት ዕውን ለማድረግ በሚያስችል አግባብ ሊቀመር ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
በደቡብ ኢትዮጲያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አዘጋጅነት በአርባ ምንጭ የተካሄደው የክልሉን የበጀት ቀመርና ተያያዥ ጉዳዮች የተመለከተ የምክክር መድረክ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ተጠናቋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉ የ2017 በጀት ዓመት የበጀት ድልድል ረቂቅ ቀመር ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችንና የክልሉን ህዝብ በጋራ የመልማት ፍላጎት ዕውን ለማድረግ በሚያስችል አግባብ ሊቀመር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማጠቃለያ ሃሳባቸው ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች መካከል፡-
- በጀትን በፍታሐዊነት ለመደልደልና ይበልጥ ለማጠናከር የመረጃ ጥራትና አደረጃጀት ሥርዓትን ማጎልበትና ማዘመን በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
- ለዚህም ከተገቢዉ ምንጭ የሚቀርቡ ግልፅ፣ ተዓማኒና ተጨባጭ መረጃዎችን ማደራጀትና በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
- የ2017 በጀት ዓመት የበጀት ድልድል ረቂቅ ቀመር በክልሉ ሕገ-መንግስት የተቀመጡ ድንጋጌዎችን እና የፌዴራል መንግስት የድጎማ በጀት ድልድል መርህን መሠረተ ያደረገና የተከተለ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
- የበጀት ድልድሉ በተጨማሪ የህዝቦች በጋራ የመልማት ፍላጎትንና የእርስ በርስ የኢኮኖሚ ትስስርን ሊያጠናክር በሚያስችል አግባብ መዘጋጀት ይኖርበታል።
- በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ልሰጠው ይገባል፡፡ ከመንግስት ከሚገኝ የበጀት ድጎማ ባላፈ ተገቢውን ትኩረት ለገቢ አሰባሰብ ተግባራት በመስጠትና የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ የዉስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
- የውስጥ ገቢን ከማሳደግ ዕኩል በጀትን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እና አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነስ በጀትን በኃላፊነትና በቁጠባ መጠቀም ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡