ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በከተማው በማድረግ ላይ ያሉትን የስራ ጉብኘት አስታከው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም አርባ ምንጭ የፍራፍሬ ቅርጫት ከመሆኗም በላይ በተፈጥሮ ፀጋ፤ በአስደማሚ የተፈጥሮ መስህብና እምቅ የቱሪዝም ሀብት የታደለች የምድር ገነት መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የአካባቢው የተፈጥሮ ስጦታ ተስፋን የሚያጭር መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢውን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ በማልማት ከመጠቀም አንጻር የሰራነው ጥቂት መሆኑ እንደ ሀገር የሚያስቆጭ ነው ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው አርባምንጭ እጅግ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን በመግለጽ ገበታ ለሀገር ለመላ ኢትዮጵያውን ይህን ድንቅ ፀጋ አልምቶ መጠቀም የሚያስችል ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በፕሮጀክቱ ድርሻ ገዝተው ኢንቨስት በማድረግ የልማቱ ተሳታፊ እና የቱሪፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አምስት ምሦሦዎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ሲሆን የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብት በማልማት ከዘረፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመረው ገበታ ለትውልድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አካባቢዎች የተመረጡ ስምንት የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት ያለመ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ሆነው በመልማት ላይ ከሚገኙ ስምንት የገበታ ለትውልድ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶች መካከል የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ፕሮጀክት አንዱ ነው።
በአካባቢው የፕሮጀክቱ መገንባት በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃትና ያሉ ሰፊ የቱሪዝም ፀጋዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማሳቻል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።