በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ተጎጂዎችን ለመደገፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጨምሮ በተለይ መላ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ባሉት ርብርብ ለአደጋው ተጎጂዎች አስፈላጊ የስብዓዊ ድጋፎችን በአግባቡ ማቅረብ ተችሏል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተጎጂዎችን የመደገፍና በዘላቂነት የማቋቋም ስራው ያለበትን ደረጃ በገመገሙበት ወቅት መላ ኢትዮጵያዊን በከፍተኛ የወገንተኝነት ስሜት እያደረጉ ባሉት ድጋፍ ለተገጂዎች ሁሉአቀፍ ድጋፎችን በተደራጀ መልኩ ተደራሽ ማድርግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በጊዜያዊ ጣቢያዎች ለተጎጂዎች በመደረግ ላይ ካለው የሰብዓዊ ድጋፍ ባለፈ የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረቱን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ላይ በማድረግ ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችንና በአካባቢው በጥናት የተለዩ የአደጋ ስጋት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ከስጋት ቀጠና ውጪ በሆነ ቦታ በአዲስ መልክ በቋሚነት የማቋቋምና ወደ ቀደመ ህይወታቸው የመመለስ ስራው ቁልፍ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ተጎጂዎችን በዘላቂነት የማቋቋሙ ስራ የቤትና የእርሻ ቦታዎችን ማመቻቸት፤ መኖሪያ ቤቶችን መስራት፤ መሠረታዊ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማሟላትን የሚያካትት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅና የጋራ ርብርብ የሚፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም የተጀመሩ የሰፈራ ቦታ ልየታና ቅዬሳ ስራዎችን ጨምሮ አስፈላጊውን ሃብት የማሰባሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በትብብር የመስራት ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋው ከ600 በላይ አባዎራዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 15 ሺህ ዜጎች በአካባቢው ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ መሆኑ ተለይቷል፡፡
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ተጎጂዎችን የመደገፉና በዘላቂነት የማቋቋም ተግባራትን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አደጋው በሰውና በንብረት ላይ አስከፊ ጉዳት ከማድረሱ ጋር ተያይዞ ተጎጂዎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራው ፈታኝና የሁሉን ድጋፍ የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው ከሁሉም አቅጣጫ ተጎጂዎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም በመደረግ ላይ ባለው ርብርብ እስካሁን ቃል ከተገባው ውጪ በተጨባጭ፤ 92 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብና ከ118 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሰብዓዊ የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
አክለውም በተለይ ምግብ ነክ የሰብዓዊ ድጋፎችን ጨምሮ የዕለት ደራሽ ድጋፍ በቂ በሚባል ደረጃ መደረጉን ገልፀው በተጎጂዎች ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው በመግለጫቸው ለተጎጂዎች በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑንም በመጥቀስ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚረዱ የፋይናንስ፤ የግንባታ ግብዓቶች፣ የእርሻ መሳሪያዎች እና ተያያዥ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት በሁሉም አካላት በመደረግ ላይ ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና በማቅረብ ተጎጂዎችንና በአካባቢው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች በቋሚነት ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ያስተላልፋል፡፡