ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ህዝቦች በአብሮነት ለመኖር የመሰረቱት አሰባሳቢና አቃፊ ሥርዓት ነው -አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአብሮነት ለመኖር የመሰረቱት አሰባሳቢና አቃፊ ሥርዓት መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዓሉ ላይ እንደገለጹት የፌደሬሽን ምክር ቤት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ለማስክበር ሰፊ ሥራ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በዋናነት እንደ አገር የብዝሃነት አያያዝ እንዲጎለብት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት ሥር እንዲሰድ ሲሰራ መቆየቱንና አሁንም እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት 18 ዓመታት በዓሉ በተከታታይ መከበሩ በአገራዊ አንድነት ግንባታ ላይ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ገልጸው፣ ይህም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በሕግ-መንግሥት ላይ የነበረ የግንዛቤ ክፍተትን ለመሙላት በዓሉ የአስተምህሮ መድረክ ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም አፌ ጉባኤው ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በዓሉ ሁሉም የአገሪቷ ህዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር እንዲሁም ለፍትህና ለነፃነት መረጋገጥ በጋራ እንዲሰሩ አድርጓል።

ይህ ደግሞ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአብሮነት ለመኖር የመሰረቱት አሰባሳቢ፣ አቃፊና አሳታፊ ሥርዓት መሆኑንም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በዓሉ መከበሩ በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ያደረገ መሆኑንም አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተከበሩ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓላት የህዝቡን አብሮነት ለማጽናት ማስቻላቸውን አፈ ጉባዔ አገኘሁ አስረድተዋል።

በመንግሥት ደረጃም ከልዩነት ይልቅ አብሮነት ለማጽናት፣ ከመራራቅ ይልቅ ለመቀራረብ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል። 

አፈ ጉባኤው በንግግራቸው በዓሉ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለሕብረ ብሔራዊ እንድነት እንዲሁም ለሕገ መንግሥት አስተምህሮ መሰረት የጣለ መሆኑን በአጽንኦት ገልፀዋል።

Leave a Reply