የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ በበይነ መረብ ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ዘጠኝ ረቂቅ ደንቦች፤ አንድ ፖሊሲ እና ሁለት አዋጆች ላይ በጥልቀት በመምከርና በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ሲሆን እነዚህም፡-
* የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት ማቋቋሚያ ደንብ፣
* የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፌንድ ማስተዳደርና ማቋቋም የወጣ ደንብ፣
* የምግብ ስረዓትና ስረዓተ ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ደንብ፣
* የማህበረሰብ ድጋፍ እና እንክብካቤ ጥምረት ማቋቋሚያ ደንብ፣
* የአርባምንጭ አካል ጉዳተኞች ታሃድሶ ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ፣
* በአርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ ሆስቴሎችን ማቋቋሚያ እና አጠቃቀም ደንብ፤
* የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና የስራ አመራር ቦርድ አደረጃጀት ለመደንገግ የወጣ ደንብ ፣
* የቱሪዝም ገቢ አሰባሰብ ደንብ ይገኙበታል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረቡ ደንቦች ላይ ተወያይቶ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በህግ ማዕቀፍ በመምራት እና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤትና አፈጻጸም በማብቃት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑን በማመን ከነማሻሻያቸው አጽድቋል፡፡
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል በሁለት ረቂቅ አዋጆች ማለትም ‘የወላይታ ግብርና ኮሌጅ ማቋቋሚያ አዋጅ’ እና ‘የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር ማቋቋሚያ አዋጅ’ እንዲሁም ‘የበጎ ፈቃደኝነት ረቂቅ ፖሊሲ’ ላይ በዝርዝር በመወያየት ለክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።
በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ የ2016 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የስራ ግምገማ እና የፕሮጀክት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ቅድመ ዝግጅት፤ የ2017 በጀት አመት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እንዲሁም ልዩ የፋይናንስ ዲጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በመወሰንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።