“መጪው ጊዜ በተገኙ ስኬቶች መኩራራት የሚፈጠርበት ሳይሆን ከሀሳብ ልዕልና ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለመሸጋገር ለቀጣይ ጉዞ ስንቅ የሚሆኑ አቅሞች ላይ በትኩረት የሚሰራበት መሆን ይኖርበታል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ”የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተከብሯል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ ከገጠመን የከፋ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ስብራት፤ በፓርቲ ውስጥ ለውጥን የመሻት ፍላጎት መኖር እና በሳል የአመራር ጥበብ ታክሎበት ደም ሳይፈስ እንደ ሀገር በእጅጉ ከተጨነቅንበት የመከራ ጊዜ ተሻግረን ለ5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቅተናል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከመገፋፋትና መጠላለፍ፣ ህብረብሔራዊነትን በተጨባጭ አቅፈን፣ በመደመር እሳቤ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅርን አስቀድመን ባለፉት አምስት አመታት በፖለቲካ ባህላችን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ በታላላቅ ስኬቶች የታጀበ፣ ቃልን በተግባር ያሳዬ፣ ሀገርን ያረጋጋ ስኬታማ ጉዞ ማድረግ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

ፓርቲያችን ብልፅግና ጥላቻን ወደ ፍቅር፣ መገፋፋትን ወደ ህብረት፣ ዕዳን ወደ ምንዳ፤ ቀውስን ወደ መረጋጋት፤ ፈተናን ወደ ምቹ አጋጣሚ እየቀየረ የመጣ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ኃያልነት እንጂ መፍረስ፣ ከፍታ እንጂ ዝቅታ አይመጥናትም በማለት፤ በፓርቲው መሪነት እና በህዝቡ ባለቤትነት ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዘገብ ችሏል ሲሉ ገልፀዋል።

ህብረ-ብሔራዊ የሆነው ብልፅግና ፓርቲ ሰላም፤ ይቅርታና ፍቅርን መርህ በማድረግ፤ በመደመር መንገድ ቃልን በተግባር እየፈፀመ ለዚህ ደረጃ ደርሷል ብለው፤ ለዚህ ስኬት አባሉ መመስገን አለባት ብለዋል።  

ፓርቲው ያደረ በክልል የመደራጀት ጥያቄ በጥበብ በመነጋገርና በመመካከር እንዲፈታ ማድረግ ችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ 32 ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ አንድ ላይ በመሆን እጅግ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ህዝበ ውሳኔ፤ በ12 ዞኖች የተዋቀረውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመስረት መቻሉንም ገልፀዋል።

የፓርቲው የአምስት አመት ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በውስጥም በውጪም በርካታ ፈተና የገጠመን ቢሆንም ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር እና ችግሮችን በመሻገር ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችለናል ሲሉ አስረድተዋል።

በለፉት 5ት ዓመታታ የተሰሩ ስራዎችን ስንቅ በማድረግ፤ ለቀጣይ ስራ የበለጠ መነሳሳት እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ተቀናጅን ኢትዮጵያን የአፍሪካ እና የአለም የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡   

ርዕሰ መስተዳድሩ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፤ መጪው ጊዜ በተገኙ ስኬቶች መኩራራት የሚፈጠርበት ሳይሆን ከሀሳብ ልዕልና ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለመሸጋገር ለቀጣይ ጉዞ ስንቅ የሚሆኑ አቅሞች ላይ በትኩረት የሚሰራበት መሆን ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባዉዲ በበኩላቸው፤ የብልጽግና ፓርቲ 5ተኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሀገር ደረጃ ለተያዘው ህልም መስፈንጠሪያ የሚሆን ነዉ ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ለቀጣይ ትግል ስንቅ በመሆናቸው በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብልጽግና በጠላትነት ከመተያየት የተሻገረ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ከፍቷል ያሉት ኃላፊው፤ ከሀገር የተሰደዱ ፖለቲከኞች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዉ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባሉ አስፈፃሚ አካላት በመካተት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የዉስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን በማስረፅ ረገድም የፓርቲው ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብጥር ለይስሙላ ከነበረበት አካታች በሆነ መንገድ በተግባር እንዲረጋገጥ መደረጉን አስረድተዋል።

በአምስት ዓመቱ ፓርቲዉ የህዝብ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ከመመለሱም በላይ በስንዴ፣ ሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ለትዉልድ የሚተላለፍ አሻራ ማኖር እንደቻለ ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመት የህልም ጉልበት ለእምርታዊ ዕድገት በሚል ከገፅታ ግንባታ ወደ ሁለንተናዊ እመርታ ለመሸጋገር በተወሰነው መሠረት በ 5 ዓመቱ የተመዘገቡ ድሎችን ወደ ላቀ ዉጤት ለመቀየር ሁሉም እንዲተጋ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት ምስረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ የፎቶ አውደ ርዕይም መርቀው ከፍተዋል፡፡  

የፎቶ አውደ ርዕዩ ባለፉት 5 ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት እና በህብተረተሰብ ተሳትፎ በማህበራዊ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በውጪ ጉዳይና ዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን የሚያስቃኝ መሆኑ ተመልክቷል። 

ብልፅግና ፓርቲ ከተመሠረተ ገና አጭር ጊዜ ቢሆንም መጠነ ሰፊ የሪፎርም ሂደት ውስጥ የሚገኝና ዓይነተ ብዙ ዕምርታ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲው ዘርፎች እያስመዘገበ ያለ ትልቅ ሀገራዊ ፓርቲ ነው፡፡ 

Leave a Reply