ተነጣጥሎ ከመኖር፣ከጥላቻ፣ ቂምና ቁርሾ አትራፊ መሆንና ማደግ ይቅርና ባሌበት መቀጠል አይቻልም። በሁሉም መስኮች ትብብርና አብሮነት የማይታዩ ከሆነ መልክና ውበታችን መታየት አይችልም። አንዳችን ለሌላችን አስፋለጊ እንደሆንን ከተረዳዳን የጋራ ልማትና እድገት እናረጋግጣለን፡፡ እስካሁን ባሳለፍነው የአብሮነት ጊዜ ብዙዎቹ ማህበራዊ ግንኙነቶቻችን፤ ወጎቻችን እና ልማዶቻችን ተወራርሰዋል ብሎም ተጋምደዋል፡፡
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው አንድነቱ እንደብረት የጠነከረ፡ በአብሮነት የተጋመደ፤ በልማት ፊት የወጣ፤ ዜጎች ሰርተው ራሳቸውን ይለውጡ ዘንድ ምቹ ሁኔታ የሰፈነበት፤ በአጭር ጊዜ እድገቱና ብልጽግናው የተረጋገጠለት ክልል እውን ለማድረግ ይህንን የተወራረሰ መስተጋብር ይበልጥ መንከባከብ እና ልዩ ጥበቃ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በተጨማሪም አብሮነታችንን የሚሸረሽሩ፤ አንድነታችንን የሚያላሉ ኩነቶችን ከማስወገድ ተሻግረን የህዝቦችን ዘመናት ያስቆጠረ የአብሮነት እሴት ለመናድ የሚከጅሉ ግለሰቦችን ሆነ ቡድኖችን የማረም ኃላፊነት ክልሉ የእኔ ነው የሚል ሁሉ ሊወጣው የሚገባው ነው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ በበዓለሲመታቸው ካደረጉት ንግግራቸው የተወሰደ፡፡