ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ሶዶ ከተማ ባደረጉት የልማት ስራዎች ጉብኝት የኢትዮ-ቺክን የለማ እንቁላል ማምረቻ ማዕከልን ጎበኝተዋል፡፡
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በክልሉ በግል ባለሀብቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በመመልከት ተቀናጅቶ መስራት የሚቻልበትን አግባብ ለማመቻቸት መሆኑም ተገልጿል፡፡
ኢትዮ-ቺክን የግል ኩባንያ በዓመት ከ70 ሚሊየን በላይ የአንድ ቀንጫጩት ለማምረት አቅዶ በመስራት ላይ የሚገኝ ኩባንያ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት እስከ 1.8 ሚሊየን የአንድ ቀን ጫጩት በማምረት ማሰራጨት መቻሉም ታውቋል፡፡
የማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ጀስቲን ቤናድ ማዕከሉን ባስጎበኙበት ወቅት ድርጅቱ በዓመት ከ70 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩት በማምረት አንድ ጫጩት ለአንድ አርሶ አደር ለማዳረስ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠ ጤናማና የበለፀገ አርሶ አደር እንዲኖር ለማስቻል እና በእንስሳት ሀብት ልማት ምርታማነትን በማሳደግ ገበያን ለማረጋጋት የሚሰራውን ስራ የማገዝ ዓላማም ያነገበ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ኩባንያው በወላይታ ማዕከል የአንድ ቀን ጫጩት ለማምረት የማስፋፍያ ስራ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአምስት የአፍሪካ ሀገሮች በመስራት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡
ኩባንያው የበለጠ ተደራሽ ለመሆን የገበያ ትስስር እና ከመኖ አቅርቦት ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ምርቱን በምፈለገው ልክ አምሮቶ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሸማቹ ከማቅረብ አንጻር ውስንነቶች ያሉበት መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተግልጿል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የኩባንያውን ጥረትና ይዞት የተነሳውን ዓላማ አድንቀው መንግስት ከገበያና መኖ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በዶሮ እርባታ ዘርፍ አመርቂ ውጤት በመመዝገብ ላይ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስትዳድሩ በአሁኑ ወቅት የአንድ ቀን ጫጩት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ማዕከሉ በበቂ ሁኔታ ሊያመርት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ኩባንያው ለገጠመው የመኖ አቅርቦት ችግር ዘላቂ መፍትሄው የመኖ ማቀነባበሪያውን እዚሁ በማምረት ኩባንያው ምርቱን በስፋት አምርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መስራት መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።