ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ሶዶ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራን ጎበኙ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ በጉብኝታቸው በወላይታ ሶዶ ከተማ በመከናወን ላይ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ስራ ጎበኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማው በመከናወን ላይ የሚገኘውን የኮርደር ልማት ስራ አድንቀው በክልሉ የከተማውን ኀብረተሰብ የልማቱ ባለቤት በማድረግ ከተሞችን ፅዱ፤ ለኑዋሪው ምቹና ተስማሚ፤ አረንጓዴ እና ለእንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በሀገሪቱ መዲና በመካሄድ ላይ የሚገኘው የኮርደር ልማት ተሞክሮን መነሻ በማድረግ በክልሉ በወላይታ ሶዶ፤ አርባ ምንጭ እና ዲላ ከተሞች የኮርደር ልማት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በሌሎች የክልሉ ማዕከላትና ከተሞች የኮርደር ልማቱን በማስፋት የሚሰራ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ለተፋጠነ የከተሞች ልማት የከተማውን ኅብረተሰብ በንቃት ማሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ባለሀብቱና የንግዱ ማህበረሰብ በዚህ ረገድ የጎላ ሚና ሊወጡ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ወጣቶች በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተሞቻቸውን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ መንግሰት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወላይታ ሶዶ ከተማን ፅዱና ውብ የማድረግ ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን  የከተማው ከንቲባ አቶ ጀገና አይዛ ገልፀዋል።

Leave a Reply