ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር በክልሉ የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የሀገራዊው የአርንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን፤ ሁምቦ ወረዳ ጋልቻ ቃራ ቀበሌ ችግኝ ተክለው አሻራቸውን በማኖር በይፋ አስጀምረዋል።    

ርዕሰ መስተዳድሩ መርሃግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታትና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀው፤ ዛሬ የምንተክለው ከናዳ ለመትረፍ፣ ከጎርፍ ለመዳን እና አረንጓዴ ምድር ለትውልድ ለማውረስ ነው  ሲሉ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልላችን የተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ምድር በእንክብካቤ ጉድለት መታመሟን የሚያሳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለህመሟ መፍትሄው የአረንጓዴ አሻራ ስራን በተደራጀ መልኩ ማከናወን እንደሆነ ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ በዛሬው ዕለት በመከናወን ላይ ባለው የአንድ ጀንበር ተከላ በክልሉ 55 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለሀገራዊው የ600 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ግብ ስኬት ጉልህ አስትዋጽኦ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማፅደቅና ማፅናት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዘንድሮ በተለየ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ክልሉ በተፈጥሮ አደጋ የተፈተነ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በክልሉ ከመቸውም ጊዜ በላይ የአረንጓዴ አሻራን የህልውና ጉዳይ በማድረግ ርብርብ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀማሪነት በ2011 ዓ.ም መርሃግብሩ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በኅብረተሰቡ ዛፍ የመትከል ባህል መሰረታዊ ለውጥ በመታየት ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ደህንነቱ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለመጪው ትውልድ ማቆየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብርም በክልሉ የደን ሽፋን ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት 22 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

በዛሬው የአንድ ጀንበር ተከላም መላው የክልሉ ህዝብ፤ ከታዳጊ እስከ አዋቂ በየአካባቢው በተዘጋጁ ችግኝ መትከያ ቦታዎች ተገኝተው በመርሃግብሩ በንቃት በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ዳግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

በክልሉ ለአንድ ጀንበር ተከላው 713 የተከላ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ 55 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀመታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች ለመትከል ዝግጀቱ ተጠናቆ ተከላው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡  

Leave a Reply