ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የተገነባ የሳሙና እና የቅባት ፋብሪካ መርቀው በመክፈት በይፋ ሥራ አስጀምረዋል

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን፤ ቦዲቲ ከተማ በማኑፋክቼሪንግ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በተሰማራ የግል ባለሀብት የተገነባ “ኤ ኤንድ ቲ” የሳሙና እና ቅባት ማምረቻ ፋብሪካን መርቀው በመክፈት በይፋ ሥራ  አስጀምረዋል።  

ፋብሪካው በወጣት ባለሀብት አቶ አብርሃም ፋንታ እና ባለቤቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተገነባ መሆኑ ታውቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፋብሪካውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከአንድ ዓመት በፊት ቆሻሻ መጣያ የነበረን ቦት በኢንቨስትመንት ለማልማት የተረከበው ወጣቱ ባለሀብት፤ ባጭር ጊዜ ይህን የመሠለ ፋብሪካ ገንብቶ ወደ ምርት ማስገባት መቻሉ፤ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው አጥረው ላስቀመጡ ባለሀብቶች አርዓያ የሆነ ተግባር በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

ወጣት ባለሀብቱ ለክልሉ ወጣቶች እና ለኢንቨሰተሮች ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባር ከመፈፀሙ ባሻገር፤ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍን በማሳደግ የውጪ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በማድረግ ላይ ያለው ጥረትን የሚያግዝ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል፡፡  

በቀጣይ ባለሃብቱ በፋብሪካው ውስጥ የምርምርና ስርፀት ማዕከል በማደራጀት፤ በክልሉ የሚመረቱ የተለያዩ ግብዓቶችን በመረከብ ለመጠቀም እና የውጪ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ፋብሪካዉ የውጪ ተኪ ምርቶችን ማምረት እንዲችል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶች ተደምረው እና ተቀናጅተው በመስራት የክልሉን ብልፅግና ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው አጥረው ያስቀመጡ ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ማልማት ሊገቡ እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በማያለሙ ባለሀብቶች ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።

Leave a Reply