ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን፤ ጨንቻ ወረዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ፤ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለይፋዊ የስራ ጉብኝቱ ጨንቻ ከተማ ሲደርሱ፤ በአካባቢው ነዋሪዎች እና በወረዳው አስተዳደር እጅግ ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጨንቻ ወረዳ ባደረጉት የልማት ስራዎች ጉብኝት፤ በኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን፤ የደቡብ ምዕራብ ቀጠና የጋሞ ጨንቻ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን፤ በጨንቻ ከተማ ጦሎላ ቀበሌ ከ72 ሄ/ር በላይ በሆነ እርሻ ላይ በማልማት ላይ የሚትገኘውን አትክልትና የአፕል የደጋ ፍራፍሬ ልማት ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ በቤተክርስቲያኗ ስር የሚገኙ ወጣቶች የመሰረቱት የሮህቦት ራስ አገዝ የአትክልትና ፍራፍሬ ማህበር፤ የጨንቻን ተራራ በአፕል የማልበስ ራዕይ በመሰነቅ፤ ከ100 በላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ከ 60 ሺህ በላይ የአፕል ችግኞች በማልማት፤ እያባዙ የማከፋፈል ስራ በመስራት ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ማህበሩ ከ24 በላይ ለደጋና ለወይና ደጋ የሚሆኑ የአትክልት እና የፍራፍሬ ዝርያዎች በማባዛት፤ ችግኞችን ከመሸጥ ባሻገር በአተካከሉ ዙርያ ስልጠና በመስጠት የማብቃትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን የሚሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህም በቤተክርስቲያኗ ወጣቶች የተመሰረተው ማህበሩ፤ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ምርታማ የአፕል ችግኞች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ፤ አርሶ አደሩ በእርሻው ላይ ምርታማ የአፕል ዝሪያዎችን በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት ከደጋ ፍራፍሬዎች ተወዳጅና እጅግ ተፈላጊ የሆነው አፕል እንደ ሀገር መነሻው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በጋሞ ዞን፤ ጨንቻ ወረዳ መሆኑን ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን፤ የጨንቻ አፕልን ለሀገር እያስተዋወቀች የምትገኝ መሆኗንም ጠቅሰው፤ ቤተክርስቲያኗ እያከናወነች ላለው አርአያ የሚሆን የአትክልትና የደጋ ፍራፍሬ ልማት ስራ ምስጋና አቅርበዋል።
ጉብኝቱ የክልሉ መንግስት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት ማግስት የተደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በግብርናው ዘርፍ በተለይ በሆልቲካልቸርና ፍራፍሬ ልማት ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፤ በክልሉ ለተመረጡ ዝሪያዎች ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ክልል ቀጣይ የሆልቲካልቸር ንቅናቄያችን፤ በተመረጡ አትክልትና ፍራፍሬ ዝሪያዎች ላይ ያተኮረ ይሆናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ ክልሉ የሚታወቅበትን የደጋ ፍራፍሬ ልማት እንደ አንድ ኢንሼቲቪ በመውሰድ፤ ጥራትና ብዛትን ባገናዘበ መልኩ፤ በኢትዮጵያ የሚታወቀውን የጨንቻ አፕል ብራንድ ምርት ለማስፋት ይሰራል ብለዋል፡፡
በክልሉ ጨንቻን ጨምሮ ጌዴኦ፤ ጋርዱላ፤ ደቡብ ኦሞ፤ ባስከቶ እና ሌሎችም ዞኖች በደጋ ፍራፍሬ ምርት እምቅ አቅም ያላቸው መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የጨንቻ አፕል ዝሪያዎችን በማሰራጨት እና ምርታማነትን በማሳደግ ከውጪ የሚገባውን የአፕል ምርት ለመተካት የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለዚህም ቤተክርስትያኗ በአካባቢው በማከናወን ላይ ያለችው የአትክልትና የፍራፍሬ ልማት አጋዥ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም ምርቱ በዚህ ሳይወሰን፤ ለሌሎች ዞኖች ተሞክሮውን በማካፈል እና ምርቱን ለማስፋት በመስራት አጋርነቷን እንዲታሳይ ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጨንቻ በነበራቸው የልማት ስራዎች ጉብኝት፤ ከአትክልትና የአፕል የደጋ ፍራፍሬ ልማት በተጨማሪ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
በዚህም ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከጨንቻ ጫኖ እና ግርጫ ኤዞ 72 ኪ/ሜ የሚሸፍን በፌዴራል መንግስት በመገንባት ላይ ያለ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት፤ በግንባታው ሂደት በተለይ ከጨንቻ ጫኖ በመገንባት ላይ ያለው መንገድ፤ በጊዜው ሰርቶ ለማጠናቀቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች በመኖራቸው ምክንያት፤ በታሰበው ልክ በፍጥነት ለመስራት እንዳልተቻለ መንገዱን በመገንባት ላይ ያለው ኪብሽ ተቋራጭ ድርጅት ገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመስክ መልከታው ወቅት፤ ተቋራጩ አሉብኝ ያላቸውን ችግሮች ባፋጣኝ በመፍታት፤ መንገዱን ሰርቶ በተያዘለት ጊዜ በማጠናቀቅ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ክፍት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይ የክልሉ መንግስት በክልሉ ያሉ፤ ሌሎች ተመሳሳይ የዘገዩ ፕሮጀክቶችን አንድ ላይ በማድረግ ከፌደራል መንግስት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመወያየት ችግሩን ለመፍታት የሚሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።