ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኦሞ ዞን፤ በዳሰነች ወረዳ ተገኝተው በቅርቡ የኦሞ ወንዝ ሙላት ያስከተለውን የጎርፍ አደጋና በአካባቢው የደቀነውን ስጋት በአካል ተገኝተው ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ በክረምት ወቅት የኦሞ ወንዝ ሙላት በአካባቢው ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ያስከተለ ሲሆን፤ አምና የከፋ ጉዳት በማድረስ ከ79 ሺህ በላይ የሚሆኑ አርብቶ አደሮችን ማፈናቀሉም ይታወሳል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመስክ ምልከታው ወቅት ዘንድሮ የወንዙ ሙላት ተመሳሳይ ጉዳት እንዳያደርስ የግድብ ስራን ጨምሮ የተለያዩ የመከላከል ስራዎች የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርን ተከትሎ የጎርፍ አደጋ ማስከተሉን ተናግረዋል፡፡
አደጋው ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመ ግብረ ኃይል ወደ ስፍራው በመንቀሳቀስ ወንዙ በሰው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመካለከል ጥረት መደረጉንም ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው፤ ከአጭር ጊዜ አኳያ በወንዙ መሙላት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በሞተር ጀልባ ጭምር በመታገዝ ህብረተሰቡን የማውጣት፤ ፈጥኖ ወደ ጊዚያዊ ማቆያ ቦታ የማስፈር እና አፋጣኝ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የማድረግ ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም የውሃው አመጣጥ ከባድ መሆኑን በመገንዘብ፤ ማሽኖችን በመጠቀም ውሃ የማፍሰስ ስራ በጊዜያዊ መፍትሄነት በመከናወን ላይ እንደሚገኝና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አብራርተዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ውሃው በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሳያደርስ ለአካባቢው ልማት መጠቀም የምንችልበትን መንገድ በጥናት በመለየት መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ወደ ወንዙ የቀረቡ ቀበሌዎችን ከወንዙ በማራቅ ማስፈርና አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት በቋሚ መፍትሄነት አቅደን የምንሰራው ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል።
የኦሞ ወንዝ ሙላት በአካባቢው ባስከተለው የዳግም መፈናቀል፤ በዘንድሮ ዓመት 2744 ያህል ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ የወንዙ ሙለት በኦሞራቴ ከተማ ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋት መደቀኑም በመስክ ምልከታው ተመልክቷል፡፡