
129ኛውን የአድዋ ድል በዓል በጋሞ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ በማድረግ ያሳለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በዞኑ የሞርካ ዋጫ ግርጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በመጎብኘት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን በሚችልበት አግባብ ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዲታ ወረዳ መክረዋል።



በምክክሩ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማትና የብልፅግና ትልማችን ስኬት የመንገድ መሠረት ልማት ቁልፍ ሚና አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሞርካ ዋጫ ግርጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በግንባታ ሂደት ያጋጠሙና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በቅርቡ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በክልሉ በመገንባት ላይ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በጋራ መገምገማቸውን ተናግረው፤ የመንገድ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አብሮ ለመስራት ከመግባባት መደረሱን ገልፀዋል፡፡



የሞርካ ዋጫ ግርጫ መንገድ ከዚህ ቀደም እጅግ አስቸጋሪና ህብረተሰቡን ለብዙ እንግልት የዳረገ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መንገዱን በመገንባት አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉት ለፌደራል መንገዶች አስተዳደር እና ለተቋራጩ ምስጋና አቅርበዋል።
አክለው በክልሉ በጥሩ ሁኔታ እየተሰሩ ያሉ መንገዶች የመኖራቸውን ያህል፤ ከካሳ አከፋፈል ጋር በተያያዘ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ ይህም መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ማነቆ እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት አዋጅ እንዲወጣ ማስገደዱን ጭምር ተናግረዋል፡፡



73 ኪሜ የሚሸፍነው የሞርካ ዋጫ ግርጫ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ከክልሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳሩ፤ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያሉ ማነቆዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት በአፋጣኝ ፍትቶ መንገዱን እስከ 2018 መጨረሻ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግስት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን እንዲችል ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር አብሮ በመስራት አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ከካሳ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመምከርና በጋራ አብሮ በመስራት መንገዱ ባፋጣኝ እንዲጠናቀቅ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንገዱ ከ7 በላይ መዋቅሮችን የሚያስተሳስር መሆኑን ገልፀው፤ የዞኑ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበርና ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ በመስራት ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለመጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልፀዋል።
የዲስትሪክቱ አመራሮች በበኩላቸው የተቀመጡ ማነቆዎች ከተፈቱ መንገዱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል ገልፀው፤ አሁን ባለበት ደረጃ ግንባታው 85 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ የአድዋን ድል በዓል በማስመልከት ትውልዱ ህብረት አንድነቱን አጠናክሮ የቀደሙ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ዘመን የማይሽረው የአድዋ ድል በልማቱ መስክ በመድገም፤ ኢኮኖሚያዊ ነፃነቷና ሁለንተናዊ ብልፅናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ማሻገር ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡