ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ “የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ በመከበር ላይ ያለውን የጳጉሜ 1 የመሻገር ቀን ተከትሎ፤ በጎፋ ዞን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለይፋዊ የስራ ጉብኝቱ፤ ጎፋ ዞን ሲደርሱ፤ በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች እና በአካባቢው ማህበረሰብ ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው፤ በገዜ ጎፋ ወረዳ በአንኮ ቀበሌ በመገኘት የሌማት ቱሩፋት አካል የሆነውን የወተት መንደር የጎበኙ ሲሆን፤ የወተት መንደሩ በቀን 600 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የሌማት ትሩፋት በእንስሳት ሀብት ልማት ህብረተሰቡን በእጅጉ ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በወተት ምርት የተሰማሩም ኑሮዋቸውን በመደጎም በህወታቸው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል፡፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ በክልሉ በመተግበር ላይ ባሉ እንሼትቮች በመመዝገብ ላይ ያለው ውጤት ክልሉን ለማሻገር አቅም በመፍጠር ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን በማጠናከር እና በማስፋት መላው ህዝባችንን አስተባብረን ክልሉን እናሻግራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተመሳሳይ፤ በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ ተገኝተው በሌማት ትሩፋት መርሃግብር፤ የእንስሳት ሀብት ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ በዛላ ወረዳ፤ ጋይላ ቀበሌ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፤ የከብት ድለባ እና ፍየል ማሞከት ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡
በጉብኝቱ በዛላ ወረዳ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር 45 የስጋ መንደሮች መመስረታቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በጋይላ ቀበሌ 3 የስጋ መንደሮች መደራጀቱም ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በወረዳው 73 የዶሮ መንደሮች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር መደራጀቱ የተገለፀ ሲሆን፤ አርሶ አደሮቹ በስጋ ልማት ምርት ውጤታማ መሆናቸው በጉብኝቱ መመልከት ተችሏል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ በቀበሌው የተመለከቱት የከብት ድለባ እና የፍየል ማሞከት ስራዎች፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳት ሀብት ልማት መስክ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ለውጦች በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለው የተደራጁ የሌማት ትሩፋት መንደሮችን አጠናክሮ አካባቢውን የስጋ ምርት ማዕከል ማድረግ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ከከብት ድለባ ስራው ጎን ለጎን አካባቢውን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ አድርጎ ማልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ማጠናከር በአካባቢው የእንስሳት ሀብት ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ በእጅጉ የሚረዳ መሆኑን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ለአርሶ አደሮቹ የገበያ ትስስር በመፍጠር በምርታቸው ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አግባብ የሚያመቻች መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጎፋ ዞን በነበራቸው የስራ ቆይታ፤ በዴማባ ጎፋ ወረዳ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት እያስገነባ የሚገኘውን የሳውላ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ያለበትን ደረጃም ተመልክተዋል።
ስድስት ሺህ ሄ/ር ላይ የሚያርፈው አዳሪ ትምህርት ቤቱ፤ ግንባታው ከተጀመረ የሶስት ወራት ዕድመ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ በመሰራት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ መፋጠን የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ በአካባቢው የትምህርት ቤቱ መገንባት ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ከማገዙም ባሻገር፤ ክልሉን በማሻገሩ ህደት የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ የተከበረውን የጳጉሜ 1 የመሻገር ቀን፤ ርዕሰ መስተዳድሩ በጎፋ ዞን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ፤ በተለያዩ ወረዳዎች ተዘዋውረው የልማት ስራዎችን በመጎብኘት እና በሚያሻግሩ ተግባራት በመሳተፍ አሳልፈዋል፡፡