ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከሃይማኖት አባቶች፣  ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ተወያዩ

“አባቶች ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባችሁ” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

“የአባቶች ሚና ለተዋበ ጠንካራ የህዝቦች አንድነት” በሚል መሪ ቃል ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከተፅዕኖ ፈጣሪ ገለሰቦች ጋር የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ በመካሄድ ይገኛል።

የውይይት መድረኩን የመሩት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በቀድሞ ክልል በህዝብ ውስጥ ተፈጥረው የነበሩ ክፍተቶችንና መሻከሮችን ለመሻር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

የእርስ በርስ ፍቅር ካለን ሰላም ይኖረናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሁሉም ነገር መሠረት የሆነው ሰላም ሲኖረን ክልላችንን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕያችንን በኅብረት ሰርተን ዕውን ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ድረስ ላሉ ስኬቶች የአባቶች ሚና ትልቁን ድርሻ ይይዛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የአባቶች ፀሎትና ምልጃ በእጅጉ ረድቶን ሰላማዊ የሆነ ክልል ሊኖረን ችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በማስፈኑ ረገድ ላበረከቱት አስተዋፅኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ማጠናከር የህዝብ ጥያቄዎችን በብቃት መመለስ የሚችል ጠንካራ ክልል እንዲኖረን ያስችላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተጋግዘን እየተመካከርን ጠንካራ ክልል እንዲኖረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ልዩነታችን ውበታችን እንጂ የምንገፋፋበች ጉዳይ ሊሆን አይገባም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ልዩነታችንን አቅምና ሀይል አድርገን ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ ይገባናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ መንግስት በክልሉ ያለን ፀጋ ተጠቅሞ በመስራት በኢኮኖሚ የበለፀገ፣ በፖለቲካ የጠነከረ ፣ ሰላሙ የተረጋገጠ ምሳሌ መሆን የሚችል ክልል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ከተመሰረተ ጀምሮ የክልሉ መንግስት በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና ሌሎች ዘርፎች የተሰሩ ዋና ዋና ተግባራትን በመድረኩ ገለፃ አድርገዋል።

ፈተናንን ወደ እድል እየቀየርን በርካታ ስራዎችን መስራት ችለናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም አባቶች ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለባችሁ ብለዋል።

ፈጥነን ስራዎቸን እንዳንሰራ እንቅፋት ለመሆን የሚጥሩ ጥቂት ሰላምን የማይፈልጉ የፖለቲካ ነጋዴዎች አባቶች ሚናቸወን በመጣት መገሰፅ እና ማስተማር እንደሚገባቸውም ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ እስከ ታችኛው መዋቅር ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን በማካሄድ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከርና ነጠላ ትርክቶችን በመታገል ኅብረትን አጠናክሮ በጋራ ሰርቶ መለወጥ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

Leave a Reply