ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ተቋሙ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እና ስራዎችን ይበልጥ ተቀራርቦ በመደጋገፍ በጋራ ለመስራት ማስቻልን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት፤ ውይይቱ ክልሉ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት ተባብሮ ለመስራትና ክፍተቶችን ለይቶ ለመፍታት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ስንቀናጅ እና ስንደመር ችግሮችን እየለየን የህብረተሰቡን ጥያቄዎች መመለስ እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር በማሻሻል ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት አኳያ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ዘርፉ ሁሌም ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ ፍላጎትን እና አቅርቦቱን አጣጥሞ የመሄድ ጉዳይ የበለጠ ሊጠናከርና ሊሰፋ የሚገባው ነው ብለዋል።
መብራት እንዲያገኙ ቃል የተገባላቸው የገጠር ቀበሌዎች አካባቢ የሚነሱ የህብረተሰቡን ጥያቄዎችን ለመመለስ ተቋሙ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ትብብር እንዲያደርግ የጠየቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት አስፋላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ አዲስ የሪፎርም ስራ በመጀመር ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ውይይቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በተመለከተ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እና ስራዎችን በጋራ ለመስራት ማስቻልን ዓላማ ያደረገ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል።
በህብረተሰቡ ለሚነሱ የመብራት ተደራሽነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በውጪ ምንዛሬ፣ እንዲሁም በበጀት ማነስ ችግር ምክንያት ተቸግረው እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ላይ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚሰሩ የተለያዩ ስራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቶችን ተንከባክቦ በመያዝ እና በመጠበቅ ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የኃይል መቋራረጦች እንዳይኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኃላፊው አሳስበዋል።