ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአርባ ምንጭ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የአረጋውያን፤ ሴቶችና ህፃናት መርጃ እና ማቋቋሚያ ማዕከል በይፋ መርቀው ከፈቱ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአርባ ምንጭ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የአረጋውያን፣ ሴቶች እና ህፃናት መርጃ እና ማቋቋሚያ  ማዕከልን በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው ወቅት የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህላችንን አጠናክረን በራሳችን አቅም በመረባረብ ድጋፍ የሚሹ እናቶች፣ አባቶች እና ወገን ዘመድ በማጣት ጎዳና የወጡ ወገኖቻችንን ሊንደግፍ ይገባ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአርባ ምንጭ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በይፋ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ትላንት ሰው የሚረዱ፤ ዛሬ የሰው እጅ የሚያዩ፤ የሚረዳቸውና የሚያግዛቸው ወገን የሌላቸው ወገኖቻችን ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ዕድሜያቸውን በሙሉ ለሰው የኖሩት ሲስተር ዘቢደር፤ ባለፉት 31 ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጎ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን በመግለፅም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

ማዕከሉ ማረፊያ ብቻ ሳይሆን ትውልድ የሚማርበት፣ ራሳቸውን ችለው ከችግር የሚወጡበት እንዲሆን ታስቦ የተገነባ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡

የወገኖቻቸውን ድጋፍን እና ጠያቂን የሚሹ ብዙ እናት አባቶች ያሉ በመሆኑ እንዲህ አይነት ማዕከላት በሌሎች የክልሉ ማዕከላትም ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሁሉም ሰው ከተባበረ ማዕከሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ በተሻለ ሁኔታ ማገልገል እንደሚችል የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ ለማዕከሉ ድጋፍ እና እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአረጋውያን መንከባከቢያ ቅጥር ግቢው ውስጥ ለሚገነባው የጎዳና ህፃናትን ማቆያ ህንፃ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይም ያኖሩ ሲሆን፤ ለማዕከሉ ግንባታ እገዛ ላደረጉ አካላት ዕውቅናም ሰጥተዋል።

የሜሪጆይ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘበደር ዘውዴ በበኩላቸው፤ ዛሬ ይሄ ማዕከል እውን የሆነው በክብር ርዕሰ መስተዳድሩ እገዛ መሆኑንን በመግለፅ የክልሉ መንግስት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይ የጎዳና ህፃናት ማቆያ እና መንከባከቢያ ማዕከል፣ የአረጋዊያን መታከሚያ የጤና ማዕከል የመገንባት ዕቅድ መያዛቸውንም ሲስተር ዘብደር ገልፀዋል።

Leave a Reply