ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ባለፈው አንድ ወር ዉስጥ በፀጥታ ግብረሃይል የተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ ከፀጥታ ኃይሎች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት፤ የፀጥታ ስራዎችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ በማጠናከር እና በየአካባቢው ያሉ የፀጥታ ስጋቶችን ለይቶ በመፍታት የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ማፅናትና አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱ በክልሉ ባለፈው አንድ ወር የተከናወኑ የፀጥታ ስራዎች የተገመገሙ ሲሆን፤ በግምገማው የክልሉን ፀጥታ አስተማማኝ ደረጃ ከማድረስ አንጻር ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸው ተመላክቷል፡፡
ለዚህም የፀጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ መስራቱ እና ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ለማፅናት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ማከናወን መቻሉ ለተመዘገበው ውጤት ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ ተገምግሟል፡፡
ከዚህም ባለፈ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሀገር መከላከያ ጋር ተቀናጅተው መስራታቸው ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ አስትዋፅኦ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በተለይ በክልሉ የፀጥታ ስጋት አለባቸው ተብሎው በተለዩ ዞኖች እና አካባቢዎች፤ የፀጥታ ኃይሉ በልዩ ትኩረት ህግ የማስከበር ስራዎችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ በቁርጠኝነት ማከናወኑ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉ ተመልክቷል፡፡
በዚህ ረገድ፤ ከዚህ ቀደም በቀድሞው ድራሼ ልዩ ወረዳ የወረዳውን አስተዳዳሪ ጨምሮ በርካታ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ አጥፊ ኃይሎችን ጨምሮ በርካታ አጥፊዎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ ለህግ ማቅረብ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በክልሉ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች እና ኮንትሮባንዲስቶች ላይ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት በተወሰዱ እርምጃዎች የአዋሳኝ አካባቢዎችን ፀጥታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራተቸውም ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የተገኙት ብርጋዴር ጀኔራል አስፋው ማመጫ፤ የቀጠናውን ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ ኃይሉ ተቀናጅቶ መስራቱ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቀጣይም ተቀናጅቶ መስራቱን የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በውይይቱ ማጠቃለያ፤ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ በማደረግ ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ የፀጥታ ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩ ዞኖች እና አካባቢዎች፤ የፀጥታ ኃይሉ ህግ የማስከበር ስራዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራትና በማጠናከር ሰላምና ፀጥታን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል፡፡