ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን የገጠር መንደሮች በአማራጭ ኢነርጂ የመብራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር ተፈራረሙ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ማዕድንና ኢነርጅ ዘርፍ፤ በተለይም የገጠሩን ህብረተሰብ በአማራጭ የኢነርጂ ኃይል የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ የልማት ትብብር ዙሪያ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት ጋር  በአርባ ምንጭ ከተማ በመወያየት የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ቻይና ከግማሽ ምዕት አመት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የቻይና መንግስት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ሲደግፍ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ድጋፍ አካል ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር ከዚህ ቀደም በክልሉ ኢንቨስትመንትና ልማት ዙሪያ ውይይት መደረጉን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዛሬው ውይይት የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን የልማት ትብብሮች በማጠናከር ወደ ተግባር ለመቀየር ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳሩ በውይይቱ በክልሉ ማዕድንና ኢነርጅ ዘርፍ፤ በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባልደረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች የገጠሩን ህብረተሰብ በአማራጭ የኢነርጂ የኃይል የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የድጋፍ ስምምነት ከኮሚቴው ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረትም የወዳጅነት ኮሚቴው በክልሉ የገጠር መንደሮች በአማራጭ የታዳሽ ኃይል የመብራት ተደራሽነት ላይ የሚሰራ የፕሮጀክት ጽ/ቤት ከፍቶ በይፋ ስራ እንደሚጀምር ተበስሯል፡፡

ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም፤ ርዕሰ መስተዳድሩ የኮሚቴው ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱን የኢኮኖሚና ልማት ልዩ አማካሪያቸው በማድረግ የሰየሙ ሲሆን፤ ሊቀ-መንበሯ የቻይና ባለሃብቶች በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም የወዳጅነት ኮሚቴው የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅምን ጨምሮ፤ ተወዳጁን የይርጋጨፈ ቡና በብራንድ ደረጃ በቻይና ገበያ የማስተዋወቅ ስራ እንዲሰራ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ከሊቀ-መንበሯ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

የኮሚቴው ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱ በዚህ ወቅት በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት መኖሩን ጠቅሰው፤ ውይይቱና ትብብሩ ይህን ግኑኝነት በልማት ትብብሮች ይበልጥ በማጠናከር የክልሉንና የሀገሪቱን ልማት ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሊቀ-መንበሯ አክለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አቅምና የመልማት ዕድል ያለው መሆኑን በክልሉ ቆይታቸው መመልከታቸውንም ጠቁመው፤ በተለያዩ የልማት ትብብሮች የክልሉን ዕድገት የሚደግፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ የተደረገው ስምምነት የክልሉን ዕድገትና ልማት በመደገፉ ረገድ ጉልህ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን ገልፀው፤ የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ኮሚቴ ከክልሉ መንግስት ጋር ለመስራት ላሳየው ከፍተኛ ተነሳሽነት እና ለሰጠው ልዩ ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply