ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን የ2017 ዓ/ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በይፋ አስጀመሩ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉን የ2017 ዓ/ም ክልላዊ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቼ ጫፋ ቀበሌ ተገኝተው አስጀምረዋል፡፡     

ርዕሰ መስተዳድሩ የበጀት ዓመቱን ክልላዊ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ለማስጀመር ጎፋ ዞን፤ ገዜ ጎፋ ወረዳ ሲደርሱ በዞኑ አስተዳደር እና በአካባቢው ማህበረሰብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡    

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልል አቀፉን የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፡- በክልሉ ያሉ ፀጋዎችንና እምቅ የመልማት አቅሞች ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

የዘንድሮን የተቀናጀ የተፈሳስ ልማት ያስጀመርንበት ስፍራ ከዚህ ቀደም በመሬት ናዳ ምክንያት እጅግ አስከፊ አደጋ ያጋጠመበት መሆኑን ያስታውሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት መራቆትና የደን መጨፍጨፍ ለናዳው መፈጠር ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።   

በተለያዩ አካባቢዎች ለሚያጋጥሙን የተፈጥሮ አደጋዎች ዋነኛ ምክንያቱ ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አባቶች ጠብቀው ያቆዩልንን ደን ጠብቀን ባለመቆየታችን ዛሬ ላይ ለችግር ተጋልጠናል ሲሉ ተናግረዋል።

የሥነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ በመስራት፣ ሀገር በቀል ዛፎችን፤ ፍራፍሬዎችን እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ጠቃሚ ተክሎችን በመትከል፣ አካባቢውን ደህንነቱ የተረጋገጠ የፍራፍሬ ኮርደር ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው፤ የተፋሰስ ልማት ሥራን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ለ30 ቀናት ብቻ የሚከናወኑ ሳይሆን፤ በባለቤትነት ስሜት ቀጣይነት ባለው አግባብ በማከናወን ተፈጥሮን መንከባከብና መጠበቅ ባህል ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ የሕዝብ ተሳትፎ በየዓመቱ እየመጨመረ የመጣ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ “የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን!” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የዘንድሮ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ፣ በተለዩ 1 ሺ 391 የማኅበረሰብ ንዑስ ተፋሰሶች፤ ከ 421 ሺህ 318 ሄ/ር በላይ መሬት በሥነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሚሸፈን መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡  

በነቃ የህብረተሰብ ተሳትፎ ለተከታታይ 30 ቀናት በሚከናወነው የዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት፤ ከ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በክልሉ የቀደሙ ምርጥ ተሞክሮዎች ተቀምረው የሚተገበሩም ይሆናል፡፡    

የክልሉ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን እውን በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ፤ የክልሉን የአፈርና የውሃ ሀብት በአግባቡ ጠብቆ መጠቀም የሚያስችል የተቀናጀ ተፋሰስ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በልዩ ትኩረት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ባለፉት አምስት አመታት በክልሉ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች፣ ከ707 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት የሸፈነ ውጤታማ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን መልሶ ማልማት ተችሏል፡፡    

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ በልዩ ትኩረት በመከናወን ላይ የሚገኙ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፤ ምርታማነትን በማሳደግም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን በመከላከሉ እና የውሃና ብዝኃ ሕይወት ሀብትን በመጠበቁ ረገድ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

የ2017 የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በተመሳሳይ በክልል በሚገኙ ሁሉም ዞኖች በህብረተሰቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በይፋ ተጀምሯል፡፡

Leave a Reply