ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ ዓመት ምሥረታን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ለመላው የክልሉ ሕዝቦች እንኳን ለታሪካዊው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ ዓመት ምሥረታ አደረሳችሁ፤ አደረሰን ያሉ ሲሆን፤ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

እንኳን ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1ኛ ዓመት ምሥረታ አደረሰን! አደረሳችሁ!

ነሐሴ 13 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፌደሬሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ የተመሠረተበት ታርካዊ ቀን!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ህዝበ ውሳኔ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደዉ ታሪካዊ የምስረታ ጉባኤ የፌደረሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ በይፋ ከተመሰረተ ዛሬ አንደኛ ዓመቱ ነው፡፡   

የሀገራዊ ለውጡ ፍሬ የሆነው ክልላችን፣ በረዥም ዘመን አብሮነትና የእርስ በርስ መስተጋብር የተጋመዱና የተሳሰሩ የኅብር ማንነቶች ባለቤት የሆኑ 32 ነባር ብሄረሰቦችና ሌሎች ሕዝቦች በጋራ የመልማት ትልማቸውን ዕውን ለማድረግ ፈቅደው የመሰረቱት ቀዳሚው የብዝኀ ሕዝቦች ክልል ነው፡፡

የክልሉ መንግስት ከምስረታ ማግስት ጀምሮ የሽግግር ጊዜና መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ በመግባት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ክልሉን ከማደራጀት ጀምሮ በሁሉም አውታሮች በተሰሩ ስራዎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡  

በሽግግር ምዕራፉ ቀዳሚ ካደረጋቸው ጉዳዮች ለክልሉ መመስረት ምክንያት የሆኑ የመልካም አስተዳደርና የግጭት መንስኤ የነበሩ የመዋቅርና ለሌሎች ያደሩ የህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ቃልን በተግባር ማረጋገጥ መቻሉ ከተመዘገቡ ስኬቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ 

ከዚህም በላይ የክልሉን ህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እና አብሮ የመልማት ትልም ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ ክልሉን በስድስት ማዕከላት አደራጅቶ፤ ተቋማዊ አሰራር በመዘርጋትና በፍጥነት ወደ ስራ በማስገባት ያልተማከለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ 

በሁሉም የመንግስት አውታሮች ስራዎችን በህግና ሥርዓት መምራት የሚያስችሉ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት በማጠናቀቅ የህግ አውጪ፤ ተርጓሚ እና አስፈጻሚ ተቋማት ብቃት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል የክልሉን የሽግግር ምዕራፍ በስኬት አጠናቆ ወደ መደበኛ የልማት ስራዎች ባጭር ጊዜ መሸጋገር ተችሏል፡፡  

የክልሉ መንግስት በመደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችም ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ፤ የክልሉን ፀጋና እምቅ አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በሁሉም የልማት መስኮች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡  

በክልሉ የልማት መሰረት ለሆነው ሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎችን በማጠናከር፤ የተለያዩ አደረጃጀቶችንና ፎረሞችን በማቋቋም እንዲሁም ነባር ሀገር በቀል ተቋማትን በመጠቀም በተሰሩ የተቀናጁ ስራዎች አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ይህም በክልሉ የተረጋጋ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምኅዳር በመፍጠር በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በሁሉም የልማት አውታሮች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አስችሏል፡፡  

በተለይ በግብርና ልማት፤ ኢንቨስትመንት፤ ቱሪዝም፤ ስራ ዕድል ፈጠራ፤ ጤና፤ የውስጥ ገቢና የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመሸፈን በተሰሩ ስራዎች የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

ክልሉ በአንድ አመት ጉዞው የተለያዩ የልማት ኢንሸቲቮችን ቀርጾ፤ መላው የክልሉን ህዝብ በንቃት በማሳተፍ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለማላቀቅ የሚያስችሉ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፤ ለአረንጓዴ ልማት ስራዎች ትኩረት በመስጠትም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከወዲሁ መሰረት የጣሉ ውጤታማ ስራዎችን መስራት ችሏል፡፡ 

ከዚህም ባሻገር የክልሉን ፀጋ በአግባቡ ተጠቅሞ ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻል እና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ በፈጠነ ጊዜ ዕውን በማድረግ የህዝቡን ሁሉ አቀፍ ልማትና ብልፅግና ለማሳካት የሚያስችል የፍኖተ ብልፅግና መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ማስገባትም ተችሏል፡፡   

የክልሉ መንግስት በቀጣይ በየዘርፉ የተጀመሩ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እና በአመራሩ ቁርጠኝነት ከዳር በማድረስ፤ የክልሉን ሕዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በጋራ የመልማት ፍላጎት ዕውን ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ የሚየደርግ ይሆናል፡፡

መላዉ ህዝባችን እንደተለመደዉ ከክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍ በአብሮነት የምንገነባዉ፣ በወንደማማችነት የምናፀናዉ፣ በፍቅር የምናሻግረዉ ክልል ስለሆነ ባለቤትነታችሁ እና አጋርነታችሁ ተጠናክሮ እንድቀጥል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

በድጋሚ እንኳን ለክልሉ ምሥረታ አንደኛ አመት በሠላም አደረሰን! አደረሳችሁ!

መጪው ጊዜ የስኬት እንዲሆን እመኛለሁ!

ፈጣሪ አገራችንና ህዝቦቿን ይባርክ፤ ይጠብቃት!

Leave a Reply