
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን ይፋዊ የስራ ቆይታ ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በቆይታቸው በዞኑ በመሰራት ላይ ያለውን የዲላ ቡሌ ሀሮ ዋጩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በመጎብኘት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን በሚችልበት አግባብ ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዲላ ከተማ መክረዋል።



ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ የክልሉን ዕድገትና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ካለው ጉልህ ሚና አንፃር፤ የክልሉ መንግስት የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካት ጋር በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲላ ቡሌ ሀሮ ዋጩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ክልሉን ከኦሮምያ ክልል ጋር የሚገናኝ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መንገዱ ካለው የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀመታ አንጻር በግንባታ ሂደት ያጋጠሙና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተነጋግሮ በጋራ በመፍታት በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡



የመንገዱ ግንባታ በተለይ ከካሳ ክፍያ እና ከኳሪ ሳይት ጋር ተያይዞ ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው ሳቢያ ግንባታውን በተቀመጠው ጊዜ ለማስከደ ተግዳሮት መፍጠሩን አያይዘው ተናግረዋል፡፡
የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ሁለቱ ክልላዊ መንግሥታት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ባጋጠሙ ማነቆዎች ዙሪያ በቀጣይ ሁለቱ ክልሎች ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንደሚሰሩ አስርድተዋል፡፡



ግንባታውን እያከናወኑ የሚገኙት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሻሸመኔ ቅርንጫፍ ኃላፊዎች በበኩላቸው፡-
ደቡብ ኢትዮጵያን እና ኦሮምያን የሚያገናኘው መንገዱ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኩል 29 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን ገልፀው፤ የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ መሰረት 23 በመቶ መድረስ ሲገባው ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት ግንባታው አሁን ላይ 7 በመቶ ብቻ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የክልሉ መንግስት በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ አብሮ በመስራት የመንገዱ ግንባታን በፍጥነት አከናውኖ በተያዘለት ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ለማስቻል ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በውይይቱ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የፌደራል መንገዶች አስተዳደር አመራሮችና የሻሸመኔ ዲስትሪክት ኃላፊዎች እንዲሁም የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።