ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዓመታዊ የግብር መክፈያ ወቅትን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ግብር የተጫነብን ግደታ ሳይሆን እንደ ዜጋ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት የምንፈጽመው የሚያኮራ የዜግነት ተግባር መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
ግብርን በወቅቱ በታማኝነት መክፈላችን እንደ ዜጋ ለሀገራችን ልማት የድርሻችንን በመወጣት ተባብረን ኢትዮጵያን ከተረጂነት የማላቀቅ ግብን ዕውን የማድረግ ታላቅ የአርበኝነት ተግባር እንፈጽማለን፡፡
ግብር በታማኝነት በመክፈል ዜጋው ለሚኖርበት ማህበረሰብ ወገንተኝነቱን፤ ሀገር ወዳድነቱንና ለሀገሩ ክብር አለኝታነቱን በተግባር ያስመሰክራል፡፡
የሚጠበቅብንን ግብር በአግባቡ መክፈላችን እጅ ለእጅ ተያይዘን የውስጥ ገቢ አቅማችንን በማጎልበት በኅብረት የጋራ ልማታችንና ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን በፈጠነ ጊዜ ለማረጋገጥ ያስችለናል፡፡
ግብርን በአግባቡ መክፈላችን በመጻሕፍትና በሌሎች የትምህርት ግብዓቶች ዕጥረት የተቸገሩ ልጆቻችንን እና የትምህርት ተቋሞቻችንን በግብዓት አጠናክረን ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ብቁ ትውልድ እንቀርጻለን፡፡
በምንከፍለው ግብር በመሠረተ ልማት ችግር ምቹ ያልሆኑ ከተሞቻችንን በሂደት ለኑሮ፤ ለንግድ፤ ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ምቹ እንዲሆኑ በማስቻል የተሻለ ውጤታማ የምንሆንበት ከባቢን እንገነባለን፡፡
በአጠቃላይ ግብርን በታማኝነት መክፈል ከምንም በላይ ለራስና ለሀገር ክብር መሆኑን በመረዳት የክልላችን ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1/2016 ዓ/ም ጀምሮ የሚጠበቅባችሁን የገቢ ግብር በወቅቱ በታማኝነት በመክፈል ኃላፊነታችሁን እንዲትወጡ ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የክልሉ መንግስት ታማኝ ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችን የሚያበረታታ መሆኑንም እየገለጽኩ በያዝነው የግብር ዘመኑ የመጀመሪያ ግብር መክፈያ ሳምንት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ፍታሃዊ ግብራችሁን በመክፈል የዜግነት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ።
የክልሉ መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ በመሰበሰብ በራስ አቅም የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም የክልሉን ገቢ ለማሳደግ የህግ ማዕቀፍ የማሻሻል፣ ግብር የሚሰውሩ አካላትን ህጋዊ መስመር የማስያዝ፣ የኮንትሮ ባንድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከልና ሌሎች የማሻሻያ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
በክልሉ በየደረጃው ያለ አመራር ለገቢ አሰባሰብ ስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻም ክልላችን ፍትሀዊ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ከመቸውም ጊዜ በላይ በ2017 በጀት አመት የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችና አዳጊ የመልማት ፍላጎቶች ደረጃ በደረጃ በመመለስ ዳግም ቃልን በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ ሲሉ ርዕሰ መስትዳድሩ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡