
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት የ2ኛ ዓመት 2ኛ ዙር መደበኛ ጉባኤ የክልሉን ሰላም ማፅናት የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ማጠቃለያ በፓርቲው 2ኛ ጉባኤ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች አንዱ ጠንካራ የሰላም ግንባታን ስራ የማጠናከር ስራ መሆኑን ገልፀው፤ በክልሉ ይህን በበላይነት ሊመራ የሚችል ጠንካራ የፀጥታ ምክር ቤት መኖሩን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ለክልላዊ የልማትና የብልፅግና ራዕይ ስኬት ሰላም መሠረት መሆኑን በማመን፥ ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት የማድረግ ግብ ጥሎ ህዝቡን ማዕከል ያደረጉ በርካታ ስራዎችን በመስራት በክልሉ አንጻራዊ ሰላምና የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ ማስፈን መቻሉን ገልፀዋል፡፡



የፀጥታ መዋቅሩን ከማጠናከር ጀምሮ ህብረተሰቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በተደራጀ አግባብ የተሰሩ በርካታ የሰላም ግንባታና የፀጥታ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተሳካ ሁኔታ ሰላም ማስፈን በመቻሉም ዘርፈ ብዙ ውጤታማ የልማት ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ የክልሉን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
በዚህም በቀጣይ 3 ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል በተጨማሪ የተገመገሙ ውስንነቶችን ለማረም ተቀናጅቶ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።


ሰላም የዕድገትና የልማት መሠረት በመሆኑ የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ለማፅናት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ከህብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አክለው የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎችን የማጠናከር እንዲሁም ከተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት ጋር የተፈጠሩ ፎረሞችን ተጠቅሞ በጋራ በመስራት የክልሉን አንጻራዊ ሰላም ማፅናት ቀጣይ የትኩረት አቅጠጫ አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የተለያዩ የሚዲያ አውታሮችን ለዕኩይ ዓላማቸው በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ በርካታ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመው፤ በቀጣይ ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ከአዋሳኝ ክልሎችና ዞኖች ጋር በቀጠናዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ጠንካራ የስራ ግንኙነት በመፍጠር በቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡


በተጨማሪም ለቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ኮንተሮባንድ ስጋት መሆኑንም ተናግረው፤ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በቀጣይ ይበልጥ የተጠናከሩ እርምጃዎችን በመውሰድ ቁጥጥሩን ማጠናከር እንደሚገባ በማሳሰብ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ በበኩላቸው፤ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ዞኖች ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አክለው በተለያዩ አካባቢዎች ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ በመስራት የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ባህላዊ የግጭት አፈታት ስረዓት ባለባቸው አካባቢዎች አንፀራዊ ሰላም መኖሩን የገለፁት ኃላፊው፤ ይህን ማህበራዊ ሀብትና እሴት አጎልብቶ በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በትኩረት መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል።