በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የ “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” ኢንሼቲቭ ከኅብረተሰቡ በተሰበሰበ ሀብት የታተሙ መፅሐፍት ሥርጭት ተጀመረ

በርዕሰ መስተደድር ጥላሁን ከበደ ሃሳብ ጠንሳሽነት ከሚያዝያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ በቆዬው ለመፅሐፍ ህትመት የሚሆን ሀብት የማሰባሰብ ዘመቻ በተሰበሰበ የገንዘብ ድጋፍ የታተሙ መፅሐፍት ሥርጭት ተጀመረ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት የሥርጭት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ በታሪካዊው ሊጋባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል፡፡

በመርሃግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልሉን በጋራ መስረትን አንደኛ ዓመታችንን ባከበርን ማግስት በክልላችን ታሪካዊ በሆነው የ “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄ የገንዘብ ድጋፍ የታተሙ መፅሐፍት ለተማሪዎችና መምህራን ለማሰራጨት በምብቃታችን ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።

የዕድገትና ብልፅግና መሰረት ትምህርት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ያለትምህርት ብቁ ሆኖ መገኝትም ሆነ ብቁ ዜጋ ማፍራት የማይቻል በመሆኑ በዋናነት የትምህርት ዘርፉን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ካልሰራን ያለምነውን ብልፅግና ዕውን ማድረግ አንችልም ሲሉ ተናግረዋል።

በክልላችን በሁሉም የትምህርት ዕርከኖች ያጋጠመን የመፅሐፍት እጥረት በማቃለል እንደ ሀገር የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማመን የጀመርነው የ “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄ ስኬት ተባብረን በኅብረት ከሰራን በሁሉም መስክ ውጤታማ መሆን እንደሚንችል ያሳዬም ነው ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው በትምህርት ላይ ያጋጠመንን ስብራት ለመጠገን በጀመርነው ጥረት ከመምህራን፤ ከወላጆች፤ ከተማሪዎች እንዲሁም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት በመስራት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የ “አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ” ኢንሸቲቪ እንዲሳካ አስተዋፆኦ ላበረከቱ፤  ካላቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ከሌላቸውም ላይ የትምህርት ጉዳይ የእኔም ጉዳይ ነው በሚል ሳይሰስቱ ድጋፍ ላደረጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ በማለትም አመስግነዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ኢንሸቲቩን በማስተባበር ለመሩ ኃላፊዎችው፤ ለቀሰቀሱ የሚዲያ አካላትና ሌሎች ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ትምህርት ቤቶችን መጠገን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማሟላት የክልሉ ሕዝብ እንዲረባረብ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለሥርጭት የበቁት መጻሕፍት ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ የታተሙ ናቸው፡፡

በዚህ መሠረት ከ220 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ የታተሙ 1 ሚሊየን 540 ሺህ 192 መጻሕፍት በመጀመሪያው ዙር ለየዞኑ ማሠራጨት ተችሏል፡፡

Leave a Reply