ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው የግብርና ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝቱ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በመከናወን ላይ ያሉ የግብርና ልማት ስራዎችን በተጨባጭ በመመልከት ጉድለቶችን ለመሙላት ዓላማ ያደረገ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ፤ በሁንቦ ወረዳ በገጠር ሥራ ዕድል ፈጣራ የተደራጁ ወጣቶች ፆሙን የከረመ መሬት በማልማት፤ ጤፍ በኩታ ገጠም በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተመልክተዋል፡፡
ወጣቶቹ በማህበር ተደራጅተው በግብርና ልማት ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ሌሎች በተግባር ማሳየታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡
ወጣቱ ከስራ ጠባቂነት ይልቅ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ ይኖርበታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጠንክረን ከሰራን ባጭር ጊዜ ከተረጂነት መላቀቅ እንደምንችል በመስክ ጉብኝቱ ያዩት ልማት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፀጋዎቻችንን ተጠቅመን የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መትጋት ይጠበቅብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ከምርት እስከ ገበያ ማመቻቸት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ዞን ባደረጉት ጉብኝት፤ በዞኑ በሆቢቻ ወረዳ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን የስራ እንቅስቃሴም የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ፤ በ”ዳኜ ዳባ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ድርጅት” የፍራፍሬ ልማት ስራ እና በግል ባለሀብቷ ወ/ሮ በረከት አደራ የለማ የኢንቨስትምንት እርሻ የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
አልሚ ባለሀብቷ በወረዳው 600 ሄ/ር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማልማት ላይ ይገኛሉ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደ ገለፁት፤ በዞኑ በግል ባለሀብቶች በተለይ በብላቴ ተፋሰስ በርካታ የኢንቨስትመንት እርሻዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን በማልማት ላይ መሆኑን በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።
የግል ባለሀብቶቹ በአከባቢው ከግብርና ልማት በተጨማሪ፤ ለአርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረጉ ረገድ እያከናወኑ ያሉት ተግባር የሚበረታታ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በፍራፍሬ ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶች፤ ከማምረት ባለፈ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተው እሴት በመጨመር የውጪ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት መስራት እንደሚገባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የክልሉን ፀጋዎች በመለየትና በማልማት ክልሉን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ገልፀዋል።
በአከባቢው በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው፤ ባለሀብቱ ለግል ጥቅሙ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀው፤ መንግስተ የብድር አቅርቦት እንዲያመቻች ጠይቀዋል።
ክልሉ በግብርናው ልማት ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ ህዝቡን ከተረጂነት ለማላቀቅ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡