
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ኢንዱስትሪ ቢሮ የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ተገኝተው እንደገለፁት፤ በክልሉ በርካታ ፀጋዎች ቢኖሩም ባለው ፀጋ ልክ በመስራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በተገቢው ልክ ከማሳደግ አኳያ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።



የንቅናቄ መድረኩ አላማም ፀጋዎችን በመለየት እና የአምራች ኢንዱስትሪው ማነቆዎችን በጋራ ተነጋግሮ በመፍታት የዘርፍን ውጤታማነት ለማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው እንደ ሀገር የገጠመንን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ዘርፉ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ውጤታማ በሆነ አግባብ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
ዘርፉ እንደ ሀገር ትልቅ ማነቆ ለሆነው የውጪ ምንዛሬ እጥረት እልባት የሰጠ መሆኑንም ጠቁመው፥ የውጪ ምርትን በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች ለመተካት የተጀመረው ጥረት አምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም እንዳለው በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑን አብራርተዋል።



የክልሉ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማጠናከርና የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ንቅናቄው አርሶ አደሩን፣ ገበያን፥ አምራቹን እንዲሁም ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል የሚያስተሳስር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዘርፉን በማጠናከር ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ፥ ተኪ ተወዳዳሪ ምርቶችን በብዛት በማምረት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ግቦችን ለማሳካትና የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ አልሚ ባለሀብቱ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ባሉ ተግዳሮቶችና በዘርፉ በሚታዩ ማነቆዎች ዙሪያ በመምከር፥ በተለይም ማነቆ ሆኖ የቆየውን የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግሮችን ተወያይቶ በመፍታትና በማመቻቸት አምራቾች ገብተው እንዲሰሩ እድሎችን ማስፋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል።
በንቅናቄው በተከፈተው ኤግዚብሽንና ባዛር ዐውደ ርዕይ የቀረቡ ምርቶች በሀገር በቀል እውቀት የተመረቱ መሆኑንም ገልፀው፤ በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በርካታ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሌሎች ዘርፎች ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን በማምረት እንዲሁም ወደ ውጪ ምርታቸውን በመላክ ጠንካራ ገቢ ያላት ሀገር ለመፍጠር መስራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ከገበያ አኳያ ያሉ ማነቆዎችንም ለመፍታት መንግስት እና አምራች ኢንዱስትሪዎች በየጊዜው እየተነጋገሩ በጋራ ችግሮችን ለመፍታት መስራት ይገባል ብለዋል።
ዘርፉ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ አምራች ኢንደስትሪዎች ያሉባቸውን አጠቃላይ ሁኔታ ከማጠን ጀምሮ በዘርፉ በየደረጃው ያሉ ችግሮችን በጥናት ላይ በተመሠረተ አግባብ ለመፍታት ከዩንቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የምርምር እና የስርፀት ስራዎች መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።



ከፋይናንስና መሰረተ ልማት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ከክልል፥ ከፌደራል እና ለሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
አመራሩ አምራች ኢንዳስትሪውን በማጠናከርና የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የውጪ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ በትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።



በተለይ የዞን አመራሮች የተደራጀ ድጋፍ በመስጠት የኢንዱስትሪ መንደሮችን ለማቋቀም መስራት ይኖርባቸዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለዚህም የለማ ቦታ አዘጋጅቶ ለአምራቹ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በልዩ ትኩረት ከተሰራበት ኢትዮጵያን ከፍ የማድረግና የማሻገር አቅም ያለው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ውጤታማነት የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ለሀገራዊ የብልፅግና ራዕይ ስኬት መስራት ይገባል በማለት ርዕሰ መስተዳድሩ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ሴክተሮች የኢኮኖሚዉ የማዕዘን ዲንጋይ በመሆን የጎላ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
አክለው መድረኩ የ”ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” የሚለው ሀገራዊ ንቅናቄ አካል በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ከሼማቹ ህብረተሰብ ጋር የሚያገናኝ ከመሆኑም ባሻገር ንቅናቀው በክልሉ ያሉ ፀጋዎችንና የመልማት አቅሞች በማስተዋወቅ አልሚ ባለሀብቱን ለመሳብ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ እስካሁን ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለባለሀብቶች መሠጠቱን ጠቅሰው፤ በንቅናቄው ከ 70 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚዎች ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።



ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ከተካሄደው ምክክር አስቀድሞ “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ኢንዱስትሪ ቢሮ የተዘጋጀ ኤግዚብሽንና የባዛር ዐውደ ርዕይ በአርባ ምንጭ ከተማ መርቀው ከፍተዋል።








