ርዕሰ መስትዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን የቦሎሶ ሶሬ ወረዳና የ ‘መጠላ ሂምበቾ’ ቀበሌ “የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የአርንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ችግኝ በመትከል አስጀምረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለዘንድሮ ክረምት የአርንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የቅድመ ተከላ ዝግጅቶች ቀደም ብለው የተጠናቀቁ ሲሆን ክልላዊ የክረምት የአርንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በይፋ አስጀምረውታል።
ርዕሰ መስተዳድሩ መርሐ-ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት የክልሉ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርና ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአረንጓደ አሻራ መርሐ-ግብር የተራቆቱ ሥነ-ምህዳሮችን መልሶ በማልማት የአካባቢ ደህንነትን ከመጠበቅ ባለፈ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ከባቢ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀማሪነት በ2011 ዓ.ም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በኅብረተሰባችን ዛፍ የመትከል ባህል መሰረታዊ ለውጥ በመታየት ላይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ደህንነቱ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለመጪው ትውልድ ማቆየት ይገባል ብለዋል፡፡
ደን መትከል፣ መንከባከብና ማፅናት የህልውና ጉዳይ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባዉ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር በክልሉ በሁለት ምዕራፎች ከ 395 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ አስታዉቀዋል።
ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን እንዲረጋገጥ የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባና ደን መትከል ብቻዉን በቂ ባለመሆኑ ችግኞችን እየተንከባከቡ ማፅደቅ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የደን እንክብካቤ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በክልሉ ጌዴኦ አከባቢ ያለዉ የዳበረ የደንና የአከባቢ ጥበቃ እንዲሁም የጥምር ግብርና ተሞክሮ መስፋት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃ/ማርያም ተስፋዬ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት አምስት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች 1 ቢሊዮን 92 ሚሊዮን ችግኞች በ 407 ሺ ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸዉን ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የክልሉ ደን ሽፋን 22 በመቶ መድረሱን አቶ ኃ/ማርያም ጠቅሰዉ በዘንድሮው የተከላ መርሃ-ግብርም 60 በመቶ የሚሆኑት የደን ችግኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከ 55 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአንድ ጀንበር የተከላ መርሃ-ግብር እንደሚተከሉ በፕሮግራሙ ተገልጿል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በዞኑ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ 103 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።
በክልሉ 395 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 55 ሚሊየን የአንድ ጀምበር ተከላ ይሆናል።
የተያዘውን ግብ ለማሳካት 430 ሚሊየን በላይ ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆኖ የችግኝ ዝግጅት ትኩረት የፍራፍሬ፣ የደንና ዘርፈ ብዙ ጠቀመታ ያላቸው ዛፎች ላይ ያተኮረ ነው።
በዘንድሮ መርሃ ግብር 134,615 ሄ/ር መሬት በደንና ጥምር ደን ዜዴዎች እንዲለማ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በበልግ ወቅት 200 ሚሊየን በላይ የተተከለ ሲሆን የአንድ ጀምበር ተከላን ጨምሮ በዚህ ክረምት 195 ሚሊየን ችግኝ ይተከላል።
የክልሉ መንግስት ለአረንጓደ አሻራና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በሰጠው ትኩረት በክልሉ የአካባቢ ደህንነትና የደን ሽፋን በማሳደጉ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡