
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የብልፅግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው ያስቀመጣጫቸው አቅጣጫዎችን በአግባቡ ከመተግበር ጋር በተያያዘ በክልሉ በየደረጃው ያለው አመራር የለውጥ መሪ ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ፓርቲያችን ብልፅግና በ2ኛ ታሪካዊ መደበኛ ጉባኤው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችንና ለኢትዮጵያ የመንሰራራት ምዕራፍ ወሳኝ ሚና ያላቸው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች፤ በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ለሀገራዊና ክልላዊ የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕይ ስኬት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት፡-
በየደረጃው ያለው አመራር እውነትን ይዞ፤ ራስን በተገቢው ዕውቀትና ክህሎት በማብቃት እንዲሁም ከሴራ ፖለቲካና ከልማድ እስረኝነት ነፃ በማድረግ እና የዲጂታል ዘመኑ ከወለደው ግልብተኝነትና በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት ዘመቻዎች የመጠለፍ አደጋ ራስን በመጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ አንድነቱን ይበልጥ አጠንክሮ የሚጠበቅበትን የለውጥ መሪነት ሚና በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፡፡
ለዚህም በመልካም ስነምግባርና ስብዕና ራስን አንፆ፤ በየወቅቱ የሚገጥሙ ወቅታዊና ጊዜያዊ ፈተናዎች በፅናት በማለፍ እንዲሁም ቀጠናዊ፤ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በውል በመገንዘብ፤ በየተሰማራበት ሴክቴር ስራዎችን በተቋማዊ ማዕቀፍና የአሰራር ስርዓት ቀጣይነታቸውን ባረጋገጠ እና ባህል ባደረገ መልኩ በቁርጠኝነት በመፈጸምና በማስፈጸም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መስራትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በለውጡ በመመዝገብ ላይ ላለው የታሪክ ዕጥፋት የራሱን አስትዋጽኦ ማበርከት መቻል ይኖርበታል፡፡
ለሚለማውም ሆነ ለሚጠፋው በየደረጃው ያለው አመራር ግንባር ቀደም ተወዳሽ አሊያም ተጠያቂ መሆኑን በመረዳት፤ ሁሌም ራስን ማዘጋጀት እና መንፈስን አፅንቶ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ለሰነቅናቸው ክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የብልፅግና ራዕይ ስኬት የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡
ለውጥ የጠንካራ ሥራና የማያቋርጥ የጋራ ጥረት ውጤት ነው!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር