በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ሁሉም ዞኖች ከሐምሌ 1 ጀምሮ ለሚጀመረው የዘመኑ የገቢ ግብር አሰባሰብ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ ዘንድሮ ለገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ከመቸውም ጊዜ በላይ የገቢ አሰባሰብ ስራዉ በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ የሚከናወን መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ ገልጸዋል፡፡
የግብር አሰባሰብ ስራው የግብር ከፋዮን ውድ ጊዜ ሊቆጥብ በሚችል መንገድ በዲጂታል አሰራር ስርዓት የታገዘ ፈጣን፤ ቀልጣፋና ምቹ እንዲሆን ለማስቻል በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በክልሉ ከ174 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን ከ112 ሺህ በላይ የሚሆኑት የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡
የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ጀምሮ ባሉት 7 ተከታታይ ቀናት በሁሉም የክልሉ ማዕከሎች፤ ዞኖችና በየደረጃው በሚገኙ የገቢ መዋቅሮች የገቢ ግብር አሰባሰብ ስራው የሚከናወን ይሆናል፡፡
በዚህም ከንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት ከ180 በላይ በሚሆኑ የታክስ ማዕከላት ለግብር ከፋዩ የአንድ መስኮት አገልግሎት በመስጠት በተቀላጠፈ አሰራር የገቢ አሰባሰብ ስራው የሚከናወን ይሆናል፡፡
የአንድ መስኮት አገልግሎት የግብር አሰባሰብ እና የንግድ ሥራ ፈቃድ ዕድሳት ሥራን በአንድነት በተቀላጠፈ አግባብ ለማከናወን ዕድል ይሰጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የግብር ውሳኔ በቴሌ ብር እንዲደርሳቸው በማድረግ ባሉበት ሆነው ግብራቸውን በዲጂታል አሰራር እንዲከፍሉ የሚደረግም ይሆናል፡፡
ወ/ሮ አለምነሽ በክልሉ በአጠቃላይ በግብር አሰባሰብ ሂደቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል የተሳለጠ እንዲሆን መደረጉ ዋናው ተጠቃሚ በተለይ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች መሆናቸውን በመግለጽ ግብር ከፋዩ ይህን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ኃላፊዋ አያይዘው ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች በክልሉ ማዕከላትና በየደረጃው በሚገኙ የገቢ መዋቅሮች የግብር መክፈያ ቦታዎች በመገኘት የሚጠበቅባቸውን ፍትሀዊ ግብር በታማኝነት እንዲከፍሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ በዘመኑ የገቢ ግብር አሰባሰብ በአጠቃላይ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።