በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ2016 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ሶዶ ከተማ በይፋ ተጀምሮ፤ በሁሉም የክልሉ ማዕከላት በተካናወኑ መርሃ-ግብሮች በልዩ ትኩረት ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል፡፡
ፍፁም ሰው ተኮር በሆነው መርሃግብሩ፤ የሀገራችንን ነባር የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴት የሚያጎለብቱ፤ አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ እና ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጎላ ሚና ያላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በዘንድሮ መርሃግብር በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከ3 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አስተባብሮ በንቃት በማሳታፍ እስካሁን በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ፤ በመተባበር ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ለአብነት፤ በክልሉ በጌዴኦ እና ወላይታ ዞኖች መላ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመቀስቀስና በነቂስ በማሳተፍ በአንድ ጀምበር ከ 4 ሺህ 5 መቶ በላይ በቶችን ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን በመገንባትና በማደስ ምሳሌ መሆን የሚችል ታላቅ ሰው ተኮር ተግባር ማከናወን ተችሏል፡፡
በጌዴኦ ዞን በአንድ ጀምበር 1 ሺ ቤቶች ለአቅመ ደካሞችና ለአረጋዊያን ለመገንባት ታቅዶ ከ1 ሺህ 8 መቶ በላይ ቤቶችን መገንባት መቻሉ በተግባር ታይቷል፡፡
በዞኑ ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተባብሮ በተካሄደ የተሳካ ዘመቻ፤ በዞኑ በ13ቱም መዋቅሮች በአንድ ጀመበር 1 ሺህ 896 ቤቶችን በመገንባት ከ 8 ሺህ በላይ የሚሆኑ አቅመ ደካማ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በወላይታ ዞን መላ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን በአንድ ጀንበር ከ2 ሺህ 600 በላይ ቤቶችን የመገንባት እና የማደስ ታላቅ በጎ ተግባር ተከናውኗል።
በዞኑ በአንድ ጀንበር ከ2300 በላይ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች በነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ በተካሄደ ንቅናቄ 2 ሺህ 6 መቶ 65 በቶችን ለአረጋዊያንና ለአቅመ ደካሞች መገንባት መቻሉ ታውቋል፡፡
በሁለቱ የክልሉ ዞኖች በአንድ ጀምበር ማሳካት የተቻለው የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤቶች ግንባታና እድሳት ለሌሎችም ምሳሌ መሆን የሚችል፤ በሁሉም የክልላችን አከባቢዎች በቀሪ ጊዜያት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ሰው ተኮር ተግባር ነው፡፡
በተያዘው ክረምት እንደ ክልል ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን በአንድ ጀንበር ገንብቶ ለማስረከብ ዕቅድ ተይዞ በመሰራት ላይም ሲሆን፤ በተለይ የወጣቱን ጉልበትና ሀሳብ በማቀናጀት በአጠቃላይ በ14 ዘርፎች የተለያዩ የበጎ ተግባራት በትኩረት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በክልላችን እያደገ የመጣው የወጣቶች የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎና ተነሳሽነት የሚበረታታ ሲሆን፤ ዘንድሮ በከፍተኛ ተነሳሽነት ወጣቱን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአረንጓዴ አሻራ፣ በአከባቢ ዉበትና ፅዳት፣ የአቅመ ደካማና አረጋዊያን ቤት የማደስና በአዲስ የመስራት ተግባራት፣ የደም ልገሳ፣ የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብና የመደገፍ፤ ዘላቂ ሰላም ግንባታና የህዝብ ለህዝብ ትስስር የማጠናከር ተግባራት፤ ገቢ አሰባሰብ እና ሌሎች አብሮነትን የሚያጎለብቱ በጎ ተግባራት በልዩ ትኩረት በንቅናቄ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
ከተባበርን ያለን ጉልበት፤ ዕውቀትና ሃብት አስተባብረን ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በራስ አቅም ችግሮቻችንን በመፍታት ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግናችንን ባጭር ጊዜ ውስጥ በእጃችን ማረጋገጥ እንደሚንችል ያመላከተም ነው፡፡
ስንተባበር እንችላለን!
በጎነት ለራስ ነው!