በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃ ግብር 55 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ64 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ተችሏል

“የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ሀገራዊው የአርንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን፤ ሁምቦ ወረዳ ተገኝተው አሻራቸውን በማኖር በይፋ ያስጀምሩት ሲሆን፤ ተከላው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በአመራሩ አስተባባሪነት እና በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ሲካሄድ ውሏል፡፡      

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጎዱ ሥነ-ምህዳሮችን መልሶ በማልማት የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅ፤  ምርታማነትን ለማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግራት ሚናው እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የክልሉ መንግስት ለአረንገዴ አሻራ መርሃግብርና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ሲሆን፤ በተለይ ዘንድሮ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን በዘለቀታዊነት ለመግታት በማለም ከመቸውም ጊዜ በላይ በበልግና በተያዘው ክረምት ከ395 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡  

የዚሁ ርብርብ አካል በሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ የዘንድሮ የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃግብር 55 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በመትከል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ለተያዘው ግብ ስኬት የድርሻውን ለማበርከት ክልሉ አስቀድሞ በቂ ዝግጅት ማድረግ ችሏል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለመርሃግብሩ ውጤታማ አፈጻጸም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፤ በተለይ በክልሉ እያጋጠመ ካለ የናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች አንጻር መላው የክልሉ ህዝብ በአንድ ጀንበር ተከላው በንቃት በመሳተፍ አሻራውን ማኖር የህልውና ጉዳይ አድርጎ በመውሰድ እንዲሳተፍ ጥሪ ከማስተላለፍም በላይ ግንዛበ በመፍጠር ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡    

በክልሉ የሀገራዊው የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃግብር በርዕሰ መስተዳድሩ አስጀማሪነት እና በመላው የክልሉ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ በዛሬው ዕለት እጅግ ውጤታማ በሆነ አግባብ ተካሄዷል፡፡   

ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ ጀንበር እስክታዘቀዝቅ በተካሄደው የተከላ መርሃግብሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ያለ አንዳች ልዩነት በነቂስ በመውጣት በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት፤ በአንድ መንፈስ ችግኝ ተከላውን ሲያካሂድ ውሏል፡፡

በዚህም በክልሉ 55 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ፤ ከዕቅድ በላይ በመፈፀም ከ 64 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በመትከል ታላቅ ስኬት እና አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በክልሉ በአጠቃላይ በ713 ተከላ ጣቢያዎች በተካሄደው የአንድ ጀንበር ተከላ መርሃግብሩ፤ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በነቂስ በመሳተፍ ለመርሃግብሩ ውጤታማነት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡

በወላይታ እና ጋሞ ዞኖች በአካል ተገኝተው አሻራቸውን በማኖር መርሃግብሩን ሲያስተባብሩ የዋሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአመራሩ እና በመላው የክልሉ ህዝብ ትብብርና የተግባር አንድነት በተደረገ የጋራ ርብርብ በክልሉ ከ64 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ ለመላው የክልሉ ህዝብ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተከላው ከ64 ሚሊዮን በላይ የደን፣ የጥምር ደን፣ የፍራፍሬ፣ የውበትና የጥላ ዛፎች እንዲሁም የመኖ ዕፅዋትና የቀርከሀ ችግኞችን ከ3 ሺሕ 944 ሄ/ር በላይ መሬት በምሸፍን ቦታ በአገር አቀፍ ደረጃ በጂኦፖርታል የመረጃ ስርዓት በተመዘገ አግባብ መትከል ተችሏል፡፡

የክልሉ መንግስት ለአረንጓደ አሻራና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በክልሉ የአካባቢ ደህንነትና የደን ሽፋን በማሳደጉ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ በመመዝገብ ላይም ይገኛል፡፡   

የዘንድሮ ተከላን ሳይጨምር በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሮች ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በ 407 ሺህ ሄ/ር መሬት ላይ መትከል የተቻለ ሲሆን፤ በዚህም የክልሉን የደን ሽፋን 22 በመቶ ማድረስ መቻሉ ታውቋል፡፡

በዛሬው የአንድ ጀንበር ተከላ በመላው ሀገሪቱ ከ 29 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊን በመርሃግብሩ የተሳተፉ ሲሆን፤ 600 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ፤ ከ 615 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል እንደ ሀገርም አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

Leave a Reply