ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኦሞ ዞን እያደረጉ ባሉት የስራ ጉብኝት፤ በደቡብ ኦሞና ኦሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት በቡስካ ደብረ ጽዮን ቅድስት ድንግል ማሪያም ዋአብነ ሙሴ ጸሊም ገዳም የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ማምረቻ ማዕከል መርቀው በመክፈት ጎብኝተዋል።
ገዳሙ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በመሰማራት አልባሳትንና ሌሎች የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች በማምረትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ገቢውን ከማሳደጉም ባሻገር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጉብኝቱ ወቅት ገዳሙ በእጃችን ብዙ ፀጋ ያለን መሆኑን የተመለከትንበት እና ፀጋዎቻችንን በአግባቡ እንዴት መጠቀም እንደሚንችል ትምህርት የወሰድንበት ነው ያሉ ሲሆን፤ ተቀናጅተን ከሰራን ባጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚንችል ያሳየም ነው ብለዋል።
የዕደ ጥበብ ውጤቶች ምርት የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘረፍ ዕድገት መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረው፤ በገዳሙ ባዩት እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት ባግባቡ በመጠቀም፤ የውጪ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰው፤ ገዳሙ በዚህ ረገድ ይበልጥ መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አክለው በቀጣይ ምርቶቹን በስፋት በማምረት ለገበያ ማቅረብና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ፤ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ የውጪ ተኪ ምርቶች ለማምረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍም ገዳሙ እያመረተ የሚገኘውን የቡስካ ማር ለገበያ ተደራሽ በማደርግ ህብረተሰቡን ከመጠቀም በተጨማሪ አካባቢን በማስተዋወቅ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከገዳሙ ልምድ እንዲቀስሙ የሚደረግ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ገዳሙ በተለያዩ የልማት ስራዎች አካባቢውን በመደገፍ ላይ መሆኑን ያደነቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይ ከዞኑ አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ በመስራት ለአካባቢው ወጣቶች የዕውቀት ሽግግር በማድረግ በስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድርግ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት የገበያ ትስስር ከመፍጠር ጀምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በአከባው የሚታዩ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዝ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገዳሙ በማህበራዊ ልማትና በመንፈሳዊ ዘርፍ የተሻለ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቀጣይ የማህበረሰቡን ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማዬሁ ባውዲ በበኩላቸው ገዳሙ ለሀገር ብልፅግና መረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ያላቸው የመንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትና የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገዳሙ ከሀይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ለሀመር እና አከባቢው ነዋሪ ቅንነትና እንግዳ ተቀባይነት ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
ገዳሙ ባጭር ጊዜ ውስጥ ስራ በመጀመር በአልባሳትና ሌሎች የዕድ ጥበብ ውጤቶችና በግብርና ምርት ውጤት እንዲያስመዘግብ ላደረጉ እንዲሁም ገዳሙን በመመስረት ሂደት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጥቷል።
በጉብኝቱ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚንስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስቴር ሙዓዝ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።