በግብርና ልማት ዘርፍ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለሚደረገው ሽግግር ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በትኩረት ከዳሰሷቸው ዘርፎች አንዱ የግብርና ልማት ዘርፍ ሲሆን፤ በግማሽ የበጀት አመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ እና ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ለ2016/17 የመኽር ወቅት እርሻ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከዕቅድ በላይ በተሰሩ ስራዎች ከ825 ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት በዓመታዊና በቋሚ ሰብሎች በማልማት ከ60 ሚሊየን ኩ/ል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ፤ እስካሁን ከ31 ሚሊየን 434 ሺህ ኩ/ል በላይ ምርት መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ቀሪው በመሰብሰብ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችን በማላመዱ ረገድ፤ በዓመታዊ ሰብሎች 211,332 ሄ/ር ማሳ በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዶ በ745 ቀበሌያት በ4,145 ክላስተር 155,281 ሄ/ር በዘር ተሸፍኖ በመልማት ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያግዙ ግብዓቶች በተለይ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር  አቅርቦትንና አጠቀቀምን ለማሻሻል በትኩረት በመሰራት ላይ ሲሆን፤ አበረታች ውጤት በመመዝገብ ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በቀጣይ በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀምን በእጅጉ ለማሻሻል የተቀናጀ ርብርብ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከቡና ልማት ጋር በተያያዘ በምርት ዘመኑ 9,074 ኪ/ግ የአካባቢና የተሻሻለ የቡና ዘር ለማቅረብ ታቅዶ 2,017 ኪ/ግ የአካባቢ እና 8,073 ኪ/ግ የተሻሻለ ዘር ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም 40,486,879 የቡና ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ 31,444,008 ማዘጋጀት መቻሉ በሪፖርቱ ቀርቧል።

ከቡና ግብይት ስራ አፈጻጸም አንጻር ለማዕከላዊ ገበያ 9,934 ቶን ቡና ለማቅረብ ታቅዶ 8,152 ቶን ማቅረብ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅመማ ቅመም ምርቶች 40,325 ቶን ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ፤ ከዕቅድ በላይ 55,777 ማቅረብ መቻሉን ገልፀዋል።

በግማሽ የበጀት አመቱ ግብርናን በማዘመን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ለመስኖ ልማትና ለሜካናይዜሽን እርሻ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱንና አርሶ አደሩ በየአካባቢው ያለውን የውሃ ሀብት ተጠቅሞ በአመት ሦሥቴ እንዲያመርት በማስቻል አበረታች ውጤት በመገኘት ላይ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በክልሉ ለእንስሳት ሀብት ልማት ትኩረት በመስጠት በተለይ የሌማት ትሩፋት መርሃግብር የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ፤ ገበያ ለማረጋጋትና ዜጎችን በስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል አግባብ በትኩረት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ውጪ በምርት ዘመኑ በሰብል ልማት፤ በቡናና ቅመማ ቅመም፤ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውሉ የቅባት አዝርቶች የተሻለ ምርታማነት መመዝገቡ በሪፖርቱ  ተዳሷል፡፡

Leave a Reply