
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በግብርና ሚንስቴር አዘጋጅነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2016 ዓ.ም የፀደቀው አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለባለድርሻ አካላት የማስተዋወቂያ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።



ርዕሰ መስተዳድሩ መድረኩ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲውን በአግባቡ ለማስፈፀምና ትግበራውን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ያለው የዘርፉ አመራር በፖሊሲው በቂ ግንዛቤ መያዝ እንዲችል በማለም መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
ሀገራችን ወደ ለውጥ እንድትገባ ካደረጓት ገፊ ምክንያቶች መካከል አንዱ በኢኮኖሚ የገጠመን ስብራት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለዚህ መፍትሄ በለውጡ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ በተወሰደ እርምጃ በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል ብለዋል።



የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለችግሮቻችን ሀገራዊ መፍትሄን የሰጠ መሆኑንም ተናግረው፥ በተለይ በአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከራስ አልፎ ወደ ውጪ መላክ በማስቻል ጭምር የታሪክ እጥፋት እንዲመዘገብ አስተዋፅኦ ማበርከት መቻሉን ገልፀዋል።
ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት የግብርና ልማት ዘርፍ ግንባር ቀደም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ያለንን የተፈጥሮና የሰው ሀይል ፀጋ ተጠቅሞ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመንና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የምግብ ልዑላዊነትን ማስከበር ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።



ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ሽግግር እውን ለማድረግ እንዲቻል አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱን ገልፀው፥ ለተግባራዊነቱ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ቀድሞ ከነበረው የግብርና ፖሊሲ ጠቃሚ የሚባሉትን በመውሰድ እና መሻሻል የሚገባቸውን ለይቶ በማሻሻል ሀገራዊ የዕድገትና ብልፅግና ትልምን ባገናዘበ መልኩ ፖሊሲው መዘጋጁትን አስረድተዋል።



አክለው ተሻሽሎ የተዘጋጀው ፖሊሲ ሀገራዊ አቅምን ተጠቅሞ ግብርናን ለማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያስችል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ፖሊሲው ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑንም ገልፀው፥ ለፖሊሲው ውጤታማ አፈጻጸም የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።



የፍላጎት፥ የምርት መጠንና አቅርቦት መጣጣም ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማነት እና የሀገራችንን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን ሚናው የጎላ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በተለያዩ መስኮች የስራ ዕድል በመፍጠር ያለንን የሰው ሀይል በአግባቡ ለማሰማራት የግብርናው ዘርፍ ያለው አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት ይገባል ብለዋል።



ለዚህም የግብርና ሜካናይዜሽንን ጨምሮ ዘርፉን በማዘመን በሁሉም መስኮች ባሉ ፀጋዎች ልክ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።
እንደ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ የክልሉን ፀጋዎች በመለየት፥ ሀገር በቀል እውቀቶችን ታሳቢ በማድረግና የተለያዩ የምርምር ተቋማትን በማቀናጀት እንዲሁም ማስፈፀሚያ ፎኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል።



እንደ ሀገር ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት በፈተናዎቾ መሃል ተኮኖ ትልልቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ተናግረዋል።
በቀጣይም በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በማሻሻል እና ምርትና ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ከተረጂነት ለመላቀቅ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ ሀሳባቸው አጠቃለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ ፖሊሲው እንደ ሀገር የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያግዝ መሆኑንን ገልፀው፤ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው የቴክኒክ እና የፖለቲካ ሂደቶችን አልፎ የትግበራ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መነሻ ሀሳብ ላይ ግምገማ በማድረግ የተዘጋጀው ሰነድ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ችግሮችን እና የመፍትሄ ሀሳቦችን አካቶ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልፀው፤ ለተግባራዊነቱ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው፡- የገጠር መሬት ደንና ተፈጥሮ ሃብት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የቴክኖሎጂ፣ የግብዓትና አገልግሎት አቅርቦት ስርዓት፣ የውሃ አጠቃቀምና አስተዳደር፣ የምርት ግብይት፣ የገጠር ልማትና መዋቅራዊ ሽግግርን ማረጋገጥ፣ የግብርና መሰረተ ልማት፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሳደግና ማጠናከር፣ የግብርናና ገጠር ልማት ፋይናንስ ስርዓት ማዘመን፣ ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት ማጠናከር፣ የግብርና አካታችነትና ዘላቂነት በፖሊሲው የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡


በመድረኩ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ፣ የግብርና ሚንስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስን ጨምሮ የክልሉ እና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።