“አመራሩ እስከታችኛው መዋቅር ወርዶ ተግባራትን በመምራት ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ዕውን ለማድረግና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ መስራት ይገባዋል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ያተኮረ የቀጣይ 90 ቀናት የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች ዕቅድና ቀጣይ አቅጣጫዎች የተመለከተ የአመራሮች የውይይት መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችንና የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ማዕከል በማድረግ የቀሪ ጊዚያት ስራዎች ዕቅድ ከልሶ የዘጠና ቀን ዕቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዉሳኔዎችን ተፈፃሚ ለማድረግ አመራሩ በበቂ ሁኔታ መግባባት፣ ዕቅድ መከለስ፣ መተግበር፣ መከታተልና ለቀጣይ ጊዜያት መዘጋጀት ይጠበቅበታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የጉባኤውን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች በአግባቡ በመተግበር ኃላፊነትን መወጣት ይገባል ብለዋል።   

በጉባኤው የተቀበልነው ታላቅ የህዝብ አደራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አምኖ አደራ ለሰጠ ህዝብ የታመነ ሆኖ በመገኘት በትኩረት መስራትና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።  

ለዚህም ወቅታዊና ጊዜያዊ ፈተናዎችን በመሻገር የውስጥና የውጪ አስቻይ ሁኔታዎችን ለይቶ ዕቅዶችን ከመከለስ ባለፈ ጠንካራ ተቋም ፍጥሮ ለውጤታማ አፈጻጸም የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።  

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ሦሥት ወራት ፓርቲዉን በአሠራርና አደረጃጀት የማጠናከር፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስር መድረኮችን የመፍጠርና ግንኙነትን የማጎልበት፣ የክልሉን ሰላም የማፅናት እንዲሁም የልማት ኢኒሼቲቮች ላይ በማተኮር የመስራት እና ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ተግባራት ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል።   

በክልሉ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ አመራሩ በግንባር ቀደምትነት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።  

አክለው ሰዉ ተኮር ተግባራትን በማከናወን እና በየዘርፉ በተቀመጡ ዕቅዶች ላይ እምርታዊ ዉጤት በማስመዝገብ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዕቅዱን ለማሳካት የአፈፃፀም ስልት እና የአመራሩ ሚና በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በማብራሪያቸው ባነሱት ሀሳብ፡- መታቀድ ባለባቸው ሀሳቦች ላይ መግባባት፣ ዕቅዱን መከለስ፣ የተከለሰውን ዕቅድ መተግበር፣ ዕቅዱ መሬት ላይ መውረዱን ስልቶችን በመንደፍ መከታተል እና መመዘን እንዲሁም ለቀጣይ ዓመት ተግባር መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዘጠና ቀን ዕቅዱን ውጤታማ በሆነ አግባብ ተግባራዊ ለማድረግ አመራሩ በቀጣይ ሶስት ወር ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ ተግባራትን በመምራት፤ በመከታተልና በመደገፍ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ዕውን ለማድረግ እና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ መስራት ዋነኛ ተግባሩ ሊያደርግ ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተያዘው ወር የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች ተፈፃሚ በሚሆኑበት አግባብ ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ በሁሉም ቀበሌያት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

አያይዘው በቀሪ ወራት የክልሉን ሕዝቦች ክልላዊ አንድነት የሚያጠናክሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ስራዎች በተጠናከረ መንገድ እንደሚካሄዱም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ከተሰጠን በላይ በመስራትና ከሚጠበቅብን በላይ በመፈፀም ኢትዮጵያን በአለም ተወዳዳሪ ለማድረግ መረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበው፤ ለዚህም ቀጣይ ዝርዝር አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

የክልሉ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎችን በአግባቡ በመፈጸም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ስልጣን ሕዝብንና ሀገርን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ በቀጣይ 90 ቀናት ከጠራ አስተሳሰብ የመነጨ የጠራ ዕቅድ በመያዝ በሁሉም ዘርፎች የተቀመጡ ዕቅዶች ላይ እምርታዊ ዉጤት ማስመዝገብ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

የጉባኤ ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ የሚተገበሩ ዕቅዶች በዝርዝር መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰው፣ በየደረጃው ያለው አመራር ባስገኘው ውጤት የሚመዘንበት አካሄድ መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

በሚቀጥሉት ሦስት ወራት በግብርና፣ በገቢ ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአረንጓዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት ኢንሺቲቮች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት አመራሩና ህዝቡ በቅንጅት እንደሚሰሩም አቶ ገብረመስቀል ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአመራሩ መካከል ቀጣይነት ያለው የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልሉ አስተባባሪ አካላት፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ዞኖች አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሦሥቱ ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች አስተባባሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Reply