‘ኢትዮጵያዊነት’ በኅብረብሔራዊቷ ደቡብ ኢትዮጵያ ይበልጥ ደምቆ ሊከበር ቀናት ቀርተዋል!

ከአመት በፊት ጅግጅጋ ላይ ቀዳሚ የብዝኃ ህዝቦች የጋራ ቤት በሆነችው ኅብራዊቷ ክልላችን ሊከበር፤ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እነሆ ጊዜው ደርሶ በውቢቷ አርባ ምንጭ በልዩ ድምቀት ሊከበር ከጫፍ ደርሷል፡፡

“ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 25 ጀምሮ ከፍ ባለ ድምቀት በሚከበረው በዓሉ፤ ኢትዮጵያዊን ከአራቱም ማዕዘናት ተሰባስበው፤ በአስደናቂ ኅብር ባህሎቻቸውና እሴቶቻቸው ታጅበው፤ በማንነት መገለጫ ቀለሞቻቸው አሸብርቀው አብሮነታቸውን ያከብራሉ፡፡

ክብረ በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንዲት እናት ሀገራቸው:- ኢትዮጵያ! ጥላ ስር ተሰባስበው፤ አሰባሳቢው የጋራ ማንነታቸው የሆነው ‘ኢትዮጵያዊነት’ በጉራማይሌው መልካቸው ይበልጥ አድምቀው በአንድነት የሚያከብሩት ነው፡፡

በርግጥም የ’ኢትዮጵያዊነት’ ቀን የሆነው ክብረ በዓሉ፤ በብዝኃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት ይበልጥ ጎልቶ የሚታይበት፤ ኢትዮጵያዊን አንድም ብዙም ሆነው ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር፤ መጻይ ዕድላቸውን በሌላ ደማቅ ታሪክ ለመጻፍ በጋራ የሚመክሩበት ነው፡፡

የኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ በኅብረብሔራዊነት በተግባር የሚገለጥበት ይሄው በዓል፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁ ስብስቦች ሳይሆኑ፤ በዘመናት አብሮነት የተዛመዱ፤ የተጋመዱ እና ባህል እሴቶቻቸውን ተወራርሰው የተሠናሠሉ መሆናቸው የሚታይበትም ነው፡፡

በዘመናት ፈተናዎች ሳይናወጥ አንድነታቸው የፀናው ህዝቦች፤ ገና ጥንት ለአንድ ዓላማ፤ በአንድ ግንባር ተሰልፈው በደምና በአጥንት በከፈሉት ዋጋ ድል ተጎናጽፈው ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ጎህ ሲቀዱ፤ የኢትዮጵያዊነት ትርጉምን ከአንድነትና አሸናፍነት አክሊል አትመው ነው፡፡

ለእኩልነትና ፍትሐዊነት በጋራ የታገሉት የሀገሪቱ ህዝቦች፤ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ሲያከብሩ የብዝኃነትን ሐምራዊ ውበት በማድነቅ ብቻ ሳይሆን፤ የአንድነትን ኃያልነትና የህልውና መሠረትነት ከትላንት የጋራ ታሪካቸው በመገንዘብ ጭምር ነው፡፡

ከህዳር 25 አስከ 29 የሰላምና የብዝኃነት ተምሳሌት በሆነው ክልላችን፤ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከመቸውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊነት በኅብረብሔራዊነት አሸብርቆ ከፍ ብሎ የሚከብርበት ነው፡፡

ኢትየጵያን የሚያሻግሩ የሰላም፣ የብዝኃነት፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የኅብረብሔራዊነት እሴቶች፣ ቱባ ባህሎችና ሥርዓቶች መገኛ በሆነው ክልላችን የሚከበረው በዓሉ፤ ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ የኅብረብሔራዊነት መሰረት ላይ የሚያንፅ ይሆናል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነጠላ ከፋፋይ ትርክቶችን በማክሰም፤ የብሔራዊነት የወል ትርክት አንግበው ቃል ኪዳናቸውን በማደስ ኅብረብሔራዊነታቸውን ሊያፀኑ፤ በሰላም መናገሻዋ አርባ ምንጭ ከቀናት በኋላ ይከትማሉ፡፡

ወትሮም እንግዳ አክባሪ፣ የሰላምና የፍቅር ሰገነት የሆነችው አርባ ምንጭ፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊን የጋራ ቤት መሆኗን ልታስመሰክር አምራና አሸብርቃ እንግዶቿን በጉጉት መጠበቅ ይዛለች፡፡

የክልላችንን ገፅታ በሚያጎላ መልኩ የሚከበረው ይህ ታላቅ ሀገራዊ ኩነት በልዩ ድምቀት ተከብሮ፤ በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና በአጠቃላይ የክልላችን ህዝቦች ሁላችንም የድርሻችንን  ልናበረክት ይገባል፡፡

ከወዲሁ እንኳን ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አደረሳችሁ! አደረሰን!

ሰናይ ሰንበት!

Leave a Reply