ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዲሽታ ጊና፡- የአሪ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ዲሽታ ጊና የአሪ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ፤ በብሄሩ የጊዜ ቀመር በወርሃ ታህሳስ መጀመሪያ ላይ በድምቀት የሚከበር ድንቅ የክልላችን እሴት ነው፡፡
በዓሉ በብሔረሰቡ ባህልና ትውፊት መሠረት፤ አዝመራው አሽቶና ፍሬ አፍርቶ በሚቀመስበትና ብሩህ ተስፋን በሚፈነጥቅበት ወቅት የሚከበር፤ አስቸጋሪው ወቅት ማለፉን በማብሰር ብሩህ ዘመንን በአዲስ መንፈስ በፍቅር የሚቀበሉበት ነው።
የተራራቁና የተነፋፈቁ የሚገናኙበትና የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት በዓሉ፤ የአሪ ህዝብ ዓመቱ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ምኞትና ምስጋና ለፈጣሪ የሚያደርስበት የምስጋና በዓል ነው።
ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የሚከበረው ዲሽታ ግና በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነ የሰላም፤ የአብሮነት፤ የመተሳሰብ እና የወንድማማችነት ተምሳሌትም ነው፡፡
በዓሉ ሌሎች ወንድም እህት ህዝቦች ጋር በአብሮነትና በአንድነት፤ የእርስ በእርስ ትስስርን በሚያጠናክር እና የወንድማማችነት እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል።
ዲሽታ ጊና የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የመደጋገፍ እሴቶችን ባቀፉ ባህላዊ ክዋኔዎች የታጀበ በመሆኑ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
በመሆኑም አባቶች ያቆዩልንን ይህን ድንቅ እሴት፤ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት በዓሉን ከነሙሉ ባህላዊ እሴቱና ትውፊቱ ጠብቆ ማቆየትና ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር መስራት ይገባዋል፡፡
በተጨማሪ የበዓሉን አከባበር በማስተዋወቅና በማጎልበት በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ!!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መልካም በዓል!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር