ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት ዲሽታ ግና፤ የኣሪ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል በኣሪ ዞን መቀመጫ በሆነችው ጂንካ ከተማ በልዩ ድምቀት ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዲሽታ ግና ለኣሪ ብሔረሰብ በኩር እና ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ የተራራቁና የተነፋፈቁ የሚገናኙበትና የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት መሆኑንም ጠቅሰው፤ ይህም የበዓሉን የሰላም ዕሴት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲሽታ ግና በዓል ፍቅርና አንድነትን ስለሚሰብክ በወንድማማቾች መካከል አብሮነትና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት እና በጎነት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በዓሉ አብሮነት፣ ፍቅርና እርስ በርስ መረዳዳትን ከመስበክ ባለፈ ህብረተሰቡን ለልማት የሚያነሳሳ ጠንካራ የሥራ ባህልን የሚያበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳሩ አያይዘው፤ የጂንካ ከተማን በአጭር ጊዜ ውብና ማራኪ ሆኖ መታየቱ አስደሳች መሆኑን ገልጸው፤ ሌሎች ከተሞች ጂንካን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ህብረተሰቡን በማስተባበር ከተማቸውን ውብና ማራኪ ለማድረግ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
ክልሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልፀው፤ ይሄው ለውጣችንና አንድነታችን የሚጎረብጣቸው አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሊከፋፍሉን ቢሞክሩ አልተሳካላቸውም ወደ ፊትም አይሳካላቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
አሪዎች፤ ጂንካዎች ውብና የአንድነት መገለጫ ተምሳሌቶች ናችሁ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እንደ ዲሽታ ግና ያሉ በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች ለህዝቦች አብሮነት፣ ሰላምና ዕድገት ትልቅ አቅም በመሆናቸው በአግባቡ ጠብቆ በማቆየት መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ ዲሽታ ግና ያሉ እሴቶችን ተጠቅመን ህብረትን በማጠናከር እና የሥራ ባህልን በማሳደግ የተጀመረውን ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ተግተን ልንሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በመጨረሻም የክልሉ ህዝብ ለከፋፋይ አስተሳሰቦች ጆሮ ሳይሰጥ አብሮነቱን በማጠናከር የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማፋጠን ጠንክሮ እንዲሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፣ ዲሽታ ግና ከዘመን መለወጫነት ባሻገር ዘርፈ-ብዙ እሴቶች ያሉት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
የዲሽታ ግና በዓል ዕርቀ-ሰላም ነው፤ የበደለ የሚክስበት፤ የተበደለ ደግሞ የሚካስበትና በእርቅ ሰላም የሚወርድበት ነው ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው የበዓሉን ትሩፋት አስረድተዋል።
ቂምና ቁርሾ ይዞ ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገር በዲሽታ ግና አይፈቀድም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዓሉ እርቅ ለማውረድና ሰላምን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲሽታ ግና እሴቶች ለሀገር ሰላም እና አብሮነት ያላቸው ሚናም የጎላ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የበዓሉ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሻገሩና በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ዞኑ የሚጠበቅበትን ሁሉ ይወጣል ብለዋል።
ምሁራን የበዓሉ ባህላዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡና በዩኔስኮ እውቅና እንዲያገኙ የድርሻቸውን እንዲወጡም ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።
በክብረ በዓሉ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በክብረ በዓሉ የኣሪን ብሔረሰብ ባህል ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁሶች አውደ ርይም ጎብኝተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የፌዴራል፣ የክልልና የዞኖች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፤ የአጎራባች ህዝቦች ተወካዮች፤ የኃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፤ እንዲሁም የጂንካ ከተማ ነዋሪዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።