ከኦሞ ወንዝ ሙላት ጋር ተያይዞ በዳሰነች ወረዳና በአካባቢው በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ የሚከሰት የጎርፍ አደጋ በጥናት ላይ በተመሰረተ አግባብ በዘላቂነት ለመፍታት ይሰራል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ ከኦሞ ወንዝ ሙላት ጋር ተያይዞ የተከሰተ የጎርፍ አደጋ በአካል ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን፤ በአደጋው ዙሪያ በኦሞራቴ ከተማ ከአካባቢው ህብረተሰብ ተወካዮች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡  

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይት መድረኩ የኦሞ ወንዝና ቱርካና ሀይቅ ሞልተው በመገናኘታቸውና ተፈጥሮአዊ ግዛታቸውን በመልቀቃቸው ምክንያት  የተከሰተ ጎርፍ በደቡብ ኦሞ ዞን፤ ዳሰነች ወረዳ በሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል።

በተለይ ከክረምት ወራት ጋር ተያይዞ በላይኛው የተፋሰሱ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ዝናብ በዝቅተኛ ስፍራ በሚገኙ የተፋሰሱ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ዜጎችን የማሸሽ ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ተፈጥሮ ከምን ጊዜውም በላይ እየፈተነን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህን ፈተና ለመሻገር የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ከዞን አስተዳደር ጋር በቅርበት በመስራት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በአካባቢው ችግሩን በጊዚያዊነት ለመፍታት ዐቢይ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቋመው እየሰሩ የሚገኙ መሆኑን ገልፀው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ የሚያሻው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በጥናት ላይ በተመሰረተ አግባብ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በህደቱም ወንዙን ከአደጋ ስጋት ምንጭነት በመግታት ሙሉ በሙሉ ለአካባቢው ዘላቂ ልማት ልውል በሚችልበት መንገድ ላይ ትኩረት የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

የክልሉ መንግስትም ከፌዴራል መንግስት፤ ከዞኑ አስተዳደር፤ በአካባቢው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች፤ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ለዘላቂ መፍትሄው በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

አደጋው በአካባቢው ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ክልሉ ተጨማሪ ማሽኖች በመጠቀም ውሃውን የማፍሰስ ተግባር በአፋጣኝ የሚያከናውን መሆኑንም ተናግረው፤ ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ያልመጡትንም በፍጥነት ማስወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው፤ በአደጋው ለተፈናቀሉ ዜጎች መደበኛ የትምህርት፤ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንዳይቋረጡ አስፈላጊው ርብርብ እንዲደረግም አቅጣጫ ሰጥተዋል። 

በአካባቢው የአደጋ ስጋት ሲያጋጥም የወረዳው አስተዳደር አስድሞ መረጃ መስጠት እንደሚገባው የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ረገድ የታዩ ክፍተቶች በቀጣይ እንዲታረሙም አስጠንቅቀዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለተደረገላቸው ሰብአዊ ድጋፍ አመስግነው ጎርፉ በየጊዜው የሚያስከትለውን ጉዳት በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ስራ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

በአካባቢው የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ተከትሎ በዳሰነች ወረዳ 139 ሺህ ሄ/ር መሬት (የወረዳው 66 በመቶ የሚሆነው ክፍል) በውሃ የተያዘ ሲሆን፤ የጎርፍ አደጋው በወረዳው ከሚገኙ 40 ቀበሌያት 34ቱን ማዳረሱ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

Leave a Reply