ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ መስራት ይገባቸዋል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት እና በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጋራ ፎረም ምስረታ በአርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ የተካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው በክልሉ መንግስትና እና በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጋራ ፎረም በይፋ ተመስርቷል።

በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ሰፊ ስራዎችን የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለው በክልሉ መንግስት እና በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የጋራ ፎረም መመስረቱ፤ ለጋራ ዓላማና ስኬት በጋራ አብሮ በመስራት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆንና ለማህበረሰቡ የላቀ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ፀጋና ከፍተኛ አቅም የሚሆን የሰው ሀይል አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይሄን ፀጋ ወደ ልማት በመቀየር ለክልሉ ልማትና ዕድገት ለማዋል በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ ክልላዊ ራዕዮችን በማሳካት የህዝቡን ተጠቃሚነት በተሻለ ለማረጋገጥ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ የማህበረሰብ ተኮር ምርምሮችን በማድረግና ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ክልሉን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 

የማህበረሰቡን የተጠቃሚነት እና የተሳትፎ ጥያቄ ለመመለስ በየተቋማቱ በተናጠል የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውንም ጠቅሰው፤ በተናጠል የሚሰሩ ስራዎችን ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀናጅቶ በጋራ በመስራት የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳሩ በተለይ በግብርና ዘርፍ በተለያዩ ምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች  በዩንቨርሲቲዎች የሚሰሩ መሆኑን በመግለፅ፤ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በጋራ አቅምን አሰባስቦ መስራት ይገባል ብለዋል።

ክልሉ በርካታ ፀጋዎችና ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የላቀ አቅም ያላቸው ምሁራንና ተመራማሪዎች ያየዙ በመሆኑ ተጋግዘንና ተደምረን በጋራ በመስራት የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ባጠረ ጊዜ በብቃት መመለስ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገር የሚጠቅሙ ተምሳሌት መሆናቸውን ማሳየት አለባቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የፎረሙ መመስረት ተቋማቱ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ህዝቡን በተሻለ ለማገልገልና ሀገርን ለመጥቀም ምቹ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በልማት ኢኒሼቲቮች በተለይም በግብርና፣ ቱሪዝም፥ በኢንዱስትሪና በማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስር በሚያጠናክሩ መስኮች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በልዩ ትኩረት መስራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋት፥ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ በመስራት እገዛ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የአርባምንጭ ዩንቨርሲቱ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የሚያደርገው ኢኮኖሚያው እና ማህበራዊ ሰው ተኮር ተግባራት እውቅና የሚሰጠው መሆኑንን ገልፀዋል፡፡

አክለው ፎረሙ መመስረቱ የክልሉን የሰላምና የብልፅግና ህልም ለማሳካት የሚረዳ እና የዩንቨርሲቲዎችን አቅም የሚያጠናክር  መሆኑንም ተናግረዋል።

መድረኩ የአርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚደንት የሆኑትን አብደላ ከማል (ዶ/ር)፥ የፎረሙ ሰብሳቢ አድርጎ በመምረጥ ተጠቃሏል።

በፎረሙ ምስረታ መርሐ ግብር በክልሉ ያሉት አራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply