“ክልሉ በቡና እና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ያለውን ፀጋ አሟጦ በመጠቀምና የምርት ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በመስራት ላይ ይገኛል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ፣ ይርጋጨፌ እና ወናጎ ወረዳዎች ተዘዋውረው የቡና ምርት አሰባሰብና ዝግጅት ያለበትን ደረጃ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ በክልሉ ከሚገኙ የግብርና ፀጋዎች መካከል ቡና እና ቅመማ ቅመም አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ ክልሉ በዘርፉ ያለውን ፀጋ አሟጦ በመጠቀምና የምርት ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በቡና ዘርፍ በተለይ የጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ እንዲሁም የአማሮ ቡናዎች በልዩ ጣዕማቸው ስመጥርና ተፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለውጪም ሆነ ለሀገር ውስጥ ገበያ እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ የቡና ምርት አሰባሰብ ሂደትን በመመልከት ድህረ ምርት ብክነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ለመከታተል እና በገበያ ትስስር ስራ ላይ በሚታዩ ማነቆዎች ዙሪያ ከአርሶ አደሩና ከቡና አምራች ባለሀብቱ ጋር ለመምከር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

የቡና ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ ወደ ብልፅግና ለምናደርገው ጉዞ ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በዘንድሮ ዓመት 230 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡናን ማልማት መቻሉንም ገልፀው፤ አሁን ላይ ከ150 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ምርት በመሰብሰብ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ከአምናው የዘንድሮ የምርት መጠን እየጨመረ እና ጥራቱ የተረጋገጠ አስተማማኝ የቡና ዝርያ ማመረት መቻሉን ያሳየ ነው ብለዋል።

በተለይ በዘር አቅርቦት፣ በማሳ ዝግጅት፣ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም የተከናወኑ ተግባራት የቡና ምርት እድገት እንዲረጋገጥ ማስቻላቸውን ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደ ሀገር የውጪ ምንዛሬ በማስገኘት ቡና የመጀመሪያውን ደረጃ እንደሚይዝ ገልፀው፤ በክልሉም ከ35 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጪ ለመላክ ታቅዶ በመሰራት ላይ መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል።

በክልሉ የቡና ልማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን መሰረታዊ ማነቆዎችን በመፍታት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመሰራት ላይ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ የሚታዩ ማነቆዎችን ከመፍታት አኳያ፤ አምራቹ ባመረተው ምርት መጠቀም እንዲችል በብሄራዊ ደረጃ ከቡና አምራቾች ጋር በመሆን ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው፤ የፋይናንስ ችግሮችን ለመቅረፍ የብድር ስረዓት ለማመቻቸት የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል። 

በቀጣይ ቡና እሴት ተጨምሮበት ለገበያ እንዲቀርብ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲጠናከሩ የሚሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው በክልሉ ያረጀ ቡና በማደስና አዲስ የቡና ችግኝ በመትከል፤ የቡና ልማት ሽፋኑን ከ228 ሺህ ሄክታር በላይ በማድረስ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ ከ35 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን መትከል መቻሉንም ጠቅሰው፤ በዚህም ምርታማነትን በአማካይ 8 ነጥብ 2 በሄ/ር እንዲሁም በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ ላይ 18 ኩንታል ማድረስ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳድሩን እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ፤ የክልሉና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply